በአዲስ አበባ ከተማ 43 ሚሊየን ብር ወጪ የደህንነት ካሜራዎች እየተገጠሙ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ በ43 ሚሊየን ብር ወጪ የደህንነት ካሜራዎች እየተገጠሙ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱልባሲጥ አህመድ፥ በአዲስ አበባ ከተማ ከቀይሽብር ሰማዕታት እስከ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አደባባይ ቁጥራቸው 140 የሆኑ የደንህነት ካሜራዎች መገጠማቸውን ተናግረዋል።

ይህም የመጀመሪያው ዙር የከተማዋ የደህንነት ካሜራ ገጠማ ስራ የመሰረተ ልማት ዝርጋታው 90 በመቶ መጠናቀቁን ያሳያል ብለዋል።

የመግጠም ስራው ተጠናቆ የሙከራ ስራ ላይ ይገኛሉ የተባሉት ካሜራዎችም በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አገልገሎት የሚጀምሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም ለፌደራል ፖሊስ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠት በከተማዋ የሚስተዋለውን የደህንነት ችግር ለማስወገድ ይረዳል ተብሏል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽኑ የአይሲቲ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ዲቪዥን ሀላፊ ምክትል ኢኒስፔክተር አንድነት ሲሳይ፥ ቴክኖሎጂው ባደጉት ሀገራት በሰፊው በስራ ላይ የሚውል መሆኑን በመጥቀስ በእኛ ሀገርም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ሙከራዎች መኖራቸውን እንስተዋል።

ቴክኖሎጂው በተለይም ወንጀልን ቀድሞ ከመከላከል አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

ስለሆነም ፕሮጀክቱ ሀገሪቱ ካላት ትንሽ በጀት ተቀንሶ የሚገነባ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ዜጎች ለራሳቸው ሀብት ትኩረት ሰጥተው መንከባከብ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎችም መሰረተ ልማቱ ላይ ጉዳት እንዳይደረስ በጥንቃቄ ማሽከርከር እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)