በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የሪል ስቴት አልሚዎችን የሚፈትሽ ግብረ-ኃይል ተቋቋመ

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የሪል ስቴት አልሚዎችን የሚፈትሽ ግብረ-ሀይል ተቋቋመ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከሪል ስቴት አልሚዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ዘርፉን የሚፈታተን በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ የሚታዩትን የአሰራር ችግሮች የሚፈትሽ ግብረ-ኃይል እንደሚቋቋም እና የሪል እስቴት ዘርፉ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ደጋፊ እንደመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ህጋዊ የሆኑትን እንደሚደግፍም አሳውቀዋል፡፡

የሚቋቋመው ግብረ-ኃይል በዋናነት በሪል እስቴት ኢንዱስትሪው ላይ የሚታዩትን ችግሮች የሚፈትሽ ሲሆን ከፕላን፣ ከካርታ፣ ከሊዝ እና መሬትን በህገ-ወጥ መንገድ አጥሮ ያስቀመጡትን እንደሚፈትሽ አሳውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በመንግስት በኩል ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮች እንደሚፈተሹ እና የከተማዋን የመኖርያ ቤት ችግር በመቅረፉ ረገድ የሪል ስቴት ኢንዱስትሪ አንዱ አማራጭ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ህግን ተከትለው ለሚሰሩ የሪል እስቴት አልሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አሳውቀዋል። (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)