በምስራቅ ወለጋ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ18 ሰዎች ህይወት አለፈ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ዛሬ እኩለ ቀን ገደማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ18 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ33 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ደህንነት ዲቪዥን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ቱሩምሳ ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ከነቀምቴ ከተማ 51 መንገደኞችን አሳፍሮ ወደ ኤቤንቱ ወረዳ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ በዞኑ ጊዳ አያና ወረዳ ለቡ ቀበሌ ሲደርስ ዛሬ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ገደማ በመገልበጡ ነው።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-29296 ኦሮ የሆነው ቅጥቅጥ ኤፍ ኤስ አር አውቶብስ አደጋው ሊደርስበት የቻለው በአደገኛ ቁልቁለት ላይ ሲጓዝ በመሪው ላይ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።

አሽከርካሪውንና ረዳቱን ጨምሮ ከሞቱት 18 ሰዎች በተጨማሪ በ10 ሰዎች ላይ ከባድ ፣በ23 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መላኩንም ተናግረዋል።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መንገደኞችም  በዞኑ ጊዳ አያና ወረዳ ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።(ኢዜአ)