“የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ” የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚደረጉ የጥምቀት በዓል አከባበሮችን ወደ መስህብነት ለመለወጥ ከወረዳዎች ጀምሮ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ካሳሁን አያሌው ተናገሩ፡፡

በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ፣ በደቡብ ክልል ደራሼ፣ በትግራይ ክልል ማይጨው እና ሌሎች አካባቢዎች የበዓል አከባበሩን የማስተዋወቅ እና ጎብኝዎች እንዲታደሙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች መሠራታቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከማይዳሰሱ ቅርሶች የሚመደበውን የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት መመዝገቡ በዓሉ ዓለም አቀፍ ዕውቅናው እንዲጨምር እና የጎብኝዎች ፍሰት እንዲያሻቅብ ይረዳልም ነው ያሉት ባለሙያው፡፡

‹‹የጥምቀት በዓል ለቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ አለው›› ያሉት አቶ ካሳሁን ሃይማኖታዊ ይዘቱን እና ፌስቲቫሎችን እንዲሁም ትዕይንቶችን ለመታደም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎች እንደሚመጡም ነው የተናገሩት፡፡ ይህም ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያበረክታል ብለዋል፡፡

በያዝነው ዓመት ባለው አንጻራዊ ሰላም ምክንያት ከአምናው በተሻለ የጎብኝዎች ፍሰት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ (አብመድ)