ሩሲያ በቀይ ባህር ዳርቻ ወታደራዊ የጦር ማዕከል ለማቋቋም ከሱዳን ጋር ተፈራረመች

ሩሲያ  በቀይ ባህር ዳርቻ አካባቢ ወታደራዊ የጦር ማዕከል እንድታቋቁም የሚያስችል ስምምነት ከሱዳን ጋር መፈራረሟ ተገለፀ፡፡

ሱዳን እና ሩሲያ በወታደራዊ መስኩ አብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈፀሙ ሲሆን የሱዳን ፓርላማ በቀይ ባህር ዳርቻ አካባቢ ሩሲያ የምትገነባውን የወታደራዊ የጦር ማዕከል አስመልክቶ የቀረበውን ረቂቅ ሀሳብ በመቀበል ስምምነት ላይ መደረሱ ነው የተነገረው፡፡

የሱዳን ፓርላማ የመከላከያ እና ደህንነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አል ሀዲ አዳም ሙሳ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት በሁለቱ ሀገራት በኩል የተፈረመው ረቂቅ ሀሳብ የሀገራቱን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ከማሳደጉ ባለፈ ሱዳንን የመከላከያ አቅም ሚያሳድግ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

አል ሃዲ በተጨማሪም ሱዳን እንደማንኛውም ሀገር በቀጠናዋ እና በግዛቷ ለሩሲያ የወታደራዊ ጦር ቀጠና እንድትገነባ የመፍቀድ መብትም አላት ነው ያሉት፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በርካታ ሀገራት የውጭ ሀገራት በግዛታቸው ወታደራዊ የጦር ማዕከል እንዲገነቡ ሲጋብዙ የቆዩ ሲሆን፣ የሱዳንም በዚሁ መልኩ መታየት ይኖርበታል ሲሉ አል ሀዲ አዳም ሙሳ ገልፀዋል፡፡

በሩሲያ በኩልም ይህ ስምምነት ተቀባይነትን ያገኘ ሲሆን የሩሲያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜዲቪዲቭ የስምምነት ረቅቅ ሀሳቡን ፈርመዋል፡፡

ይህ ስምምነት እንዲፈረም መነሻ የሆነው ባለፈው አመት ማለትም በፈረንጆቹ 2018 ሩሲያ ባዘጋጀችው የአለም ዋንጫ የታደሙት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽ ከፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር በመገናኘት በወታደራዊ መስኩ በጋራ ለመስራት ከተስማሙ በኋላ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በ2017 እንደፈረንጆች በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ ተገናኝተውም በወታደራዊ መስኩ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ካውሩ በኋ ላ በተለይ ሩሲያ የሚሳኤል እና ተዋጊ ጀቶችን ለሱዳን ለማቅረብም ተስማምተው ነበር፡፡

የኦማር ሀሰን አል በሽር መንግስት በምዕራባዊያን የተጣለባቸውን ማዕቀብ ተከትሎ ኢኮኖሚያቸው በመጎዳቱ አሁን ላይ ከሱዳናዊያን የስልጣን ይልቀቁ ጥያቄዎች ቢበረክቱም፤ ሩሲያ ብቸኛዋ አጋር ሆና ቀጥላለች፡፡

የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግኑኝነትም በአመት እስከ 400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡ (ምንጭ:አልጀዚራ)