ቻይና እና ግብጽ የሁለትዮሽ ትብብር ለማሳደግ ተስማሙ

ቻይና እና ግብጽ በሁሉም መስኮች ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማሳደግ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

ባለፉት አመታት ቻይናና ግብፅ በመሪዎቻቸው አመራርነት ሁለንተናዊ የስትራቴጂክ አጋርነታቸውን ማጎልበት መቻላቸውን በካይሮ ጉብኝት ያደረጉት የቻይናው ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ ያንግ ጄቺ ተናግረዋል፡፡

መልዕክተኛው ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ባደረጉት ውይይት የሀገራቱን ሁሉን አቀፍ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጎልበት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

ተወካዩ የግብጽ ጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ተፈጻሚ በሚሆንበት አግባብ ላይ ለመምከር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ያንግ ጄቺ ሀገራቱ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የሚያደርጉት ትብብር የበለጠ እንደሚጠናከር ፤በፖለቲካው መስክ የጋራ መተማመናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና የሁለቱንም ሀገራት ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እርስ በእርስ እንደሚደጋገፉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቻይና የዘረጋችውን የአንድ መንገድ አንድ መቀነት ኢኒሼሪቭን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሁለንተናዊ የስትራቴጂክ አጋርነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

ያንግ ከፕሬዝዳንት ሲሲ ጋር ባደረጉት ውይይት የቻይናው ፕሬዝዳት ሺጂፒንግ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ እና በስምንተኛው የቻይና አረብ ሀገራት የትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ያቀረቧቸውን አዳዲስ ኢኒሼቲቮች በሚመለከት ሀሳቦችን አንስተዋል፡፡

ቻይና በአረቡ አለም እና በአፍሪካ ዋነኛ ሀገር ከሆነችውና በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ከምትረከበው ግብጽ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማሳገድ ዝግጁ መሆኗን የጠቆሙት መልዕክተኛው በአፍሪካ ቻይናና በቻይና አረብ ሀገራት የትብብር ፎረሞች ላይ የተደረሱ ስምምነቶችን ተፈጻሚ ለማድረግና ትብብሮቹን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሰሲሲ በበኩላቸው ረጅም አመታትን ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ከፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ ጋር የደረሱትን ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

ግብጽ የአፍሪካ ህበረት ለቀመንብርነትን በምትረከብበት ሰአት የቻይናና የአፍሪካ ሀገራትን እንዲሁም የቻይናና የአረብ ሀገራትን ግንኙነት ለማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትሰራለች ብለዋል፡፡

ያንግ በካይሮ በነበራቸው ቆይታ ከግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ከግብጹ ፕሬዝዳንት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ እና ከአረብ ሊግ ዋና ጸሀፊ ጋር ተገናኝተው መክረዋል፡፡/ሲጂቲኤን/