የአፍሪካ መሪዎች በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አደረጉ

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር እና የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሀማት ተሳትፈዋል።

መሪዎቹ ውይይታቸውን ሲጀምሩ ስብሰባውን የጠሩት የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር እና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በእንዲህ ዓይነቱ አፍሪካዊ ችግር ላይ አህጉሪቱ የራሷን መፍትሄ እንድትሰጥ ጥረት መደረጉ የውጭ ወገኖች በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዳይገቡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ በሀገሪቱ እውቅና በተሰጣቸው ተቋማት በኩል መፈታት አለበት ነው ያሉት።

ሊቀመንበሩ በስብሰባ ላይ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ እንዲሳተፉ ቢጋበዙም በሀገሪቱ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ መገኘት እንዳላስቻላቸው በማንሳት የአፍሪካ ህብረት የሚያስቀምጣቸው መፍትሄዎች ካሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ በበኩላቸው የአህጉሪቱ መሪዎች ለእንዲህ ዓይነቱ አፍሪካዊ ችግር መፍትሄ ለማምጣት መሰብሰባቸው በመካከላቸው ያለውን ትብብር የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ 38 ነጥብ 57 በመቶ ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አውጆ ነበር።

ተቀናቃኛቸው ማርቲን ፋዩሉ ደግሞ 34 ነጥብ 8 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸው ቢገለፅም ውጤቱን እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የገለጸ ሲሆን ይህ ሁኔታ ቀድሞም በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የኖረችውን ሀገር ጨምሮ አካባቢውን ወደ ሌላ ቀውስ እንዳይከት ስጋት ፈጥሯል።