በህንድ የሚገኙት ሮሂንጋዊያን ሙስሊሞች ከሂንዱ ብሄርተኞች የተነሳባቸዉን ተቃዉሞ ተከትሎ ወደ ባንግላዲሽ እየተሰደዱ ነው

በማይናማር የተፈፀመባቸዉን የማንነት ጥቃት ሸሽተዉ በህንድ የሚገኙት ሮሂንጋዊያን ሙስሊሞች ከሂንዱ ብሄርተኞች የተነሳባቸዉን ተቃዉሞ ተከትሎ ወደ ባንግላዲሽ እየተሰደዱ ነው፡፡

አልጀዚራ ዛሬ ያስነበበዉ ዜና እንዳመላከተዉ አዲሱ የፈረንጆቹ አመት ከተጀመረ ወዲህ ብቻ ከ1 ሺህ 300 የሚበልጡ ሮሂንጋዊያን በህንድ የተጋረጠባቸዉን ስጋት በመሸሽ ድንበር አቋርጠዉ ወደ ባንግላዲሽ መትመም ጀምረዋል።

ሮሂንጋዊያኑን ለስደት የዳረጋቸዉ መነሻም በህንዳዊያን ብሄርተኞች የተነሳባቸዉ ተቃዉሞና የሀገራችንን ይልቀቁ ጥያቄ መሆኑ ተነግሯል።

በቅርብ ጊዜያት የህንድ መንግስት በስደት በሀገሪቱ የሚገኙትን የሮሂንጋ ማህበረሰቦች ወደ ማይናማር እንዲመለሱ ማድረጉ  ከተባበሩት መንግስታትና አለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ነቀፋን አስከትሎበታል።

በተለይም ሮሂንጋዊያኑ በማይናማር ከፍተኛ ግድያ ደርሶባቸዉ ህይወታቸዉን ለማትረፍ ወደ አጎራባች ሀገራት መሰደዳቸዉ እየታወቀ የህንድ መንግስት ሮሂንጋዊያኑን ወደ ማይናማር መመለሱ አለም አቀፍ ህግጋትንም ጭምር የጣሰ ተግባር ነዉ በሚል ሀገሪቱን አስወቅሷታል።

የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮንቬንሽን አባል እንዳልሆነች የሚነገርላት ህንድ ባለፈዉ 2018 የፈረንጆቹ አመት ብቻ 230 ሮሂንጋዊያንን በቁጥጥር ስር ዉለዉ ለእስር መዳረጋቸዉና ከብሄረተኛ ህንዳዊያን ዛቻና ማስፈራራያ እየደረሰባቸዉ መሆኑ በሀገሪቱ ያላቸዉን ቆይታ እንዳሳጠረዉ በመነገር ላይ ነዉ።

በተለይም ብሄረተኞቹ ህንዳዊያን ሮሂንጋዊያኑ ሀገራችንን በፍጥነት ይልቀቁ የሚል ጠንካራ ጥያቄን ማቅረባቸዉ ስጋቱ እንዲያይል አድርጎታል።

የደቡብ እስያ የሰብዓዊ መብት ማዕከል እንዳስታወቀዉ ባለፈዉ አመት ብቻ የህንድ መንግስት ሮሂንጋዊያን ስደተኞችን ለስቃይ እየዳረገ መቆየቱን ይፋ አድርጓል። በዚህም ከ200 በላይ ሮሂንጋዊያን ለእስር መዳረጋቸዉን ተቋሙ ይፋ አድርጓል።

አሁን በህንድ የተጋረጠባቸዉ አደጋ ስጋት ዉስጥ የከተታቸዉ ሮሂንጋዊያንም ጓዜን ማቄን ሳይሉ ለስደት እግራቸዉን ወደ ባንግላዲሽ አንስተዋል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከፈረንጆቹ ጥር 3 ጀምሮ ወደ ባንግላዲሽ የሚተሙት ስደተኛ ሮሂንጋዊያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተመላክቷል።

የፈረንሳዩን የዜና ወኪል ኤ ኤፍ ፒን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበዉ ከሆነ እስከ ትላናትናዉ እለት ብቻ ከ300 አባ ወራዎች የተወጣጡ 1 ሺህ 300  ስደተኞች የባንግላዲሽን ምድር ረግጠዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ፊራስ አል ካቲብ ኤጀንሲያቸዉ ጉዳዩን እንደሚያዉቀዉ ገልጸዉ፣ በቅርብ ሳምንታት ዉስጥ ወደ ባንግላዲሽ ሲያመሩ የነበሩ ስደተኞች በፖሊስ ተይዘዉ ኮክስ ባዛር ወደተሰነዉ ትልቁ የአለም የስደተኛ ካምፕ መላካቸዉን ይፋ አድርገዋል።

እስካሁንም 40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሮሂንጋዊያን በስደት በህንድ  ሲኖሩ ነበር ተብሏል።

ሆኖም ህንድ በሮሂንጋዊያን ላይ እያደረሰች ባችዉ በደል ምክኒያት አመነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ትችት እያቀረበባት እንደሚገኝ ተነግሯል።

ሮሂንጋዊያን ሙስሊሞች በማንነታቸዉ ምክንያት ለአመታት በማያንማር ከፍተኛ ግድያና ስቃይ ሲደርስባቸዉ የኖሩ ማህበረሰቦች ሲሆኑ ባለፈዉ የፈረንጆቹ ነሃሴ 2017 በሀገሪቱ ራኪን ግዛት በተቀሰቀሰ ፀረ ሮሂንጋ ተቃዉሞ ምክንያት በርካቶቹ ተገድለዋል፣ ገሚሶቹም ለስደት ተዳርገዋል። 

ቀድሞ በባንግላዲሽ በስደት ላይ ከነበሩት 300 ሺህ ሮሂንጋዊያን በተጨማሪ 720 ሺህ  ሮሂንጋዊያን ባለፈዉ አመት ከማይናማር ተሰደዋል፡፡/አልጀዚራ /