በአዲስ አበባ አንዲት እናት 6 ህፃናትን በሰላም ተገላገሉ

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት 30 ዓመት እናት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል 6 ህፃናትን በሰላም ተገላግለዋል።

ወይዘሮዋ 3 ወንድና 3 ሴት ህፃናትን በተደረገላቸው ቀዶ ጥገና ነው የተገላገሉት።

ህፃናቱ ከ700 እስከ 980 ግራም የሚመዝኑ ሲሆን፥ አዲስ የተወለደ አንድ ጤናማ ህፃን ክብደት በአማካኝ እስከ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም እንደሆነ ከህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በጨቅላ ህፃናት ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገኙት ስድስቱ ህፃናት በህክምና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለ1 ወር ያክል ተኝተው ክትትል ሲያደርጉ የቆዩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት እናት በሆስፒታሉ ባለሞያዎች ለተደረገላቸው እንክብካቤ ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ በተመሳሳይ አንድ እናት 5 ሴት ህፃናት በሰላም መውለዳቸውን የጨቅላ ህፃናት ፅኑ ህሙማን ክፍል ባለሞያ ሲስተር አስካለ አሰፋ ይናገራሉ።

ከ3 ወራት ቀደም ብሎ በቀዶ ጥገና የተወለዱት ህፃናት ክብደት ከ800 እስከ 1200 ግራም እንደነበረም ነው ሲስተር አስካለ አስታውቀዋል።

ከተወለዱት 5 ህፃናት 4ቱ አሁንም በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉም ብለዋል።

እንዲህ አይነት ከተለመደ ውጭ የሆነ ክስተት የመፈጠር እድሉ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የሆስፒታሉ ባለሞያዎች ገልፀዋል።(ኢቢኮ)