ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ተጨማሪ ጥረት እና ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ተባለ

ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ቢቻልም ከዚህ በላይ ለመቀነስ ተጨማሪ ጥረት እና ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

የጤናማ እናትነት ወር በአለም ለ30ኛ ጊዜ በአገራችን ለ13ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

የዘንድሮው የጤናማ እናትነት ወር በዓል “በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል” በሚል መሪ ቃል በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ስነ ስርአቶች ተከብሯል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ከጤና ኬላዎች እስከ ሆስፒታሎች በስፋት በመገንባት፣ እንዲሁም አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እስከ ስፔሽያሊስቶች በማሰልጠን ለህብረተሰቡየሚሰጠው የጤና አገልግሎት እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዚሁ መሰረት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ብዙ መንገድ ተጉዘናል ያሉት ዶ/ር ሊያ በየአመቱ የሚመዘገበው የእናቶች ሞት በፊት ከነበረው በከፍተኛ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡

 ሆኖም አሁንም በአመት ከ11ሺህ እስከ 13ሺህ የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ እንደሚሞቱ መረጃዎች ስለሚያሳዩ ተጨማሪ ጥረት እና ቀጣይነት ያለው ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሊያ ጨምረው እንደተናገሩት የደም ልገሳን ልማድ በማድረግ ደም የሚፈሳቸው እናቶችን በደም እጥረት ከሚደርሰውን ሞት ለመታደግ ሁሉም ዜጋ ደም በመለገስ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም ከ50 በመቶ በላይ ለሚሆን የእናቶች ሞት ምክንያት ከወሊድ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ተናግረው በተለይ በደም መፍሰስ የሚያልፈው የእናቶች ህይወት ቀዳሚ ቦታን እንደሚይዝ አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየሁ በበኩላቸው እንደተናገሩት ባለፉት አመታት የጤና አገልግሎት እና ተደራሽነት ረገድ እንዲሁም የህብረተሰብን ንቃተ ጤና ከፍ ማድረግ ላይ ብዙ ሥራዎች ተሰርቷል ብለዋል፡፡

የእናቶችን ጤና ለማሻሻል ሰፊ ርብርብ ቢደረግም አሁንም ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር አበባው ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎችም የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ እና ከሞት ለመታደግ የሚያስችሉ አስተዋፅኦዎችን በማበርከት የእናትን ውለታ መክፈል አለበት ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ትልቅሰው ይታያል ናቸው፡፡

ከበዓል አከባበር ስነ ስርዓቱ በኋላ በባህር ዳር ከተማ ውስጥ የሚገኙ የጤና ተቋማት ከጤና ጥበቃ እና ከአጋር ድርጅቶች በተገኙ እንግዶች ተጎብኝተዋል፡፡