ከ20 ዓመታት ታሪክ መማር የተሳናቸው ፖለቲከኞች

ከአህመድ አባ ቢያ

አንድ የማህበረሰባዊ ሳይንስ ምሁር በየትኛውም ማህበረሰብ ዘንድ ጠንካራ ትስስርና አንድነት እውን ሊሆን የሚችለው መላው ዜጋ በአንድ የፖለቲካ ምህዳር ወይም ተቋማዊ መዋቅር ስር አብሮ ለመኖር  ቁርጠኛ ፍላጎት ካለው ብቻ ነው ይላሉ፡፡ እኚህ ምሁር የደረሱበት ይህ ድምዳሜ ትክክለኛ መሆኑን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለይም አፍሪካ ውስጥ ከቀኝ ግዛት ዘመን በኋላ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ታሪክ በአንክሮ ያጤነ  ማንም ሰው ያለምንም ማቅማማት ሊቀበለው ይችላል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የሚባሉት የአፍሪካ አገራት በርካታ ቋንቋዎችን የሚናገሩና የተለያዩ ባህሎች ያሏቸው ህዝቦች የሚኖሩባቸው ናቸው፡፡  ያም ሆኖ ግን ቀኝ ገዢዎች የአንድ ቋንቋንና ማህበረሰባዊ አመለካከት ልእልናን በማግነን በሚያመቻቸው መልኩ የተከሉት ስርዓት የቀኝ ግዛትን ባለፉ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የተስተዋለ የታሪክ ክስተት መሆኑን የታሪክ መዛግብት ይገልፃሉ፡፡ እነዚህ ህዝቦች ቋንቋን፣ ባህልንና መሰል የማንነት መብት ጥያቄዎቻቸውን በተለያየ መንገድ ቢያነሱም ቀኝ ገዢዎቻቸው ለአገዛዝ የሚያመቻቸውን ቋንቋን ጨምሮ በአንድ የተለየ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ስነ ልቦናዊ አስተሳሰብ የመዋጥ (Assimilation) ስርዓትን ከመዘርጋት ውጭ በተቆጣጠሯቸው አገራት ለሚገኙ ህዝቦች የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህላዊ እሴቶች ቦታ አይሰጡም  ነበር፡፡

አገራቱ ከቀኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላም ቢሆን ስልጣኑን የተረከቡት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት የፖለቲካ ሰዎች ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በየአገሮቻቸው ለማስተዋወቅ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ቀደም ሲል ምእራባዊያኑ ገዢዎቻቸው በተከሉላቸው ስርዓት ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳያካሄዱ ነበር ህዝቦቻቸውን ለመምራት የሞከሩት፡፡ አንዳንዶቹም ዴሞክራሲን ለማስፈን ያደረጓቸው ጥረቶች በምእራባዊያኑ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተመሰረቱና አብዛኛዎቹም ሙሉ በሙሉ ከእነርሱው ላይ የተቀዱ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

ያም ሆኖ ግን የአፍሪካ አገራት ከሌላው የዓለም ክፍል በበለጠ መጠን በርካታ ቋንቋዎች የሚነገርባቸውና የተለያዩ ባህሎች ያሉባቸው አገራት ከመሆናቸው አኳያ በእነዚህ አገራት ውስጥ ይነሱ የነበሩት የዴሞክራሲና የፖለቲካ መብት ጥያቄዎች ሊመለሱና ሊስተናገዱ የሚችሉበት አቅጣጫ በፀባዩም ሆነ በወቅታዊነቱ ከምእራቡ ዓለም ፍፁም የተለዩ ነበሩ፡፡

አዲሶቹ መሪዎች በተለያዩ የአፍሪካ ህዝቦች ዘንድ ያለማቋረጥ ይቀርቡ የነበሩ የብሄረሰብና የማንነት ጥያቄዎችን ኋላ ቀርና አቆርቋዥ አስተሳሰብ፤ በቀኝ ግዛት ዘመን ቅኝት የተተከሉትንና የአሃዳዊ አመለካከቶችን  ደግሞ የእድገትና ለውጥ መሳሪያዎች ብሎ በመፈረጅ የእድገት መሳሪያ ነው ያሉትን የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ህዝቦቻቸው ላይ ለመጫን ሞከሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ስርዓቶቹ በአገራቱ መንግስታትና ህዝቦቻቸው መካከል የሚፈለገውን መተማመን መገንባት አልቻሉም፤ ህዝባዊ ተቀባይነትንም አላገኙም፡፡

ይህም በየአገራቱ የከፉ የፖለቲካ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት ሆነ፡፡  መንግስታቱም የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ከመጣር ይልቅ አንባገነናዊ መንገድን መከተል ጀመሩ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በእነዚህ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች እጣ አያሌዎችን ለህልፈትና ለከፋ ድህነት የዳረገ የእርስ በእርስ ግጭት ሆነ፡፡  እነዚህ ጥያቄዎች ያልተፈቱባቸው የአፍሪካ አገራት አሁንም ድረስ በግጭት ውስጥ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በቀኝ ያልተገዛች አገር ብትሆንም እየተወራረሱ አገሪቱን ለመቶዎች አመታት ያስተዳደሩት ንጉሳዊያን ቤተሰቦች አማካኝነት እላይ ከተጠቀሱት የአፍሪካ አገራት ጋር ተመሳሳይ የሆነ እውነትን አስተናግዳለች፡፡ በርካታ ቋንቋዎች፣ የተለያዩ ሐይማኖቶች፣ ባህሎችና የህይወት እሳቤዎች ባሉባት ኢትዮጵያ አንድ ቋንቋና ሐይማኖት ብቻ እንዲገንና መላው ዜጋም በዚህ ቅኝት ውስጥ ሆኖ እንዲመራ ያላሰለሰ ጥረት ተደርጓል፡፡

ይህ ሌሎችን የመዋጥ (assimilate) የማድረግና በአንድ ቋንቋና ሐይማኖት የመተካት ጥረት የተፈለገውን አሃዳዊ ስርዓት ከማምጣት ይልቅ በተለያዩት የአገሪቱ ብሄሮችና ህዝቦች ዘንድ ቅሬታን እያባባሰ አመፅንና ተቃውሞን ነበር የወለደው፡፡ በዚህም ሳቢያ የማንነትና ሌሎች ዴሞከራሲያዊ ጥያቄዎችን ያነገበው ይህ አመፅም በንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አገዛዝ ይመራ የነበረውን ዘውዳዊ ስርዓት የገረሰሰ አብዮት አስከተለ፡፡

ያም ሆኖ አብዮቱ አሰቃቂ በሆነ የኃይል እርምጃ ጭምር በወታደራዊ ቡድን ተቀለበሰ፡፡ ይህ ስርዓትም ለአያሌ ዓመታት ሲቀርብ ለነበረው የማንነትና ሌሎች ህዝባዊ የመብት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎቹን በኃይል መደፍጠጥን በመከተሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶቻቸውን ለማስከበር የትጥቅ ትግልን ጨምሮ በተለያየ መልኩ የጀመሩትን ተቃውሞ ቀጥለውበት አምባገነኑን የደርግ ስርዓት መገርሰስ ቻሉ፡፡ በኢህአዴግ መሪነትም አገሪቱ ለማንነታቸው፤ለዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች መከበርና በአጠቃላይም ለነጻነታቸው ነፍጥ ባነሱ የተለያዩ ብሔሮችና ሕዝቦች ተወካዮች አመራር ስር ዋለች፡፡

በዋነኝነት ኢህአዴግ በወቅቱ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት በማንም ወታደራዊ ኃይል አይገረሰስም ይባል የነበረውን ግዙፍ ወታደራዊ ስርዓት ማስወገድ የቻለው ትግሉ ውስጥ የተሳተፈው የግንባሩ ሰራዊት ህዝባዊ መሰረትን የተላበሰና ጠንካራ ህዝባዊ ድጋፍ ስለነበረው መሆኑን በአገሪቱ ታሪክ ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ እናም ይህ ህዝባዊ ጥያቄ በአግባቡና በፍጥነት ምላሽ ካላገኘ አገሪቱ አሁንም ወደማያቋርጥ ግጭትና ትርምስ ውስጥ ትገባለች፤ አሊያም ተበታትና እንዳልነበረች ትሆናለች የሚለው እምነት በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በግልፅ ይስተጋባ ጀመር፡፡

ራሱን የቻለ ነፃ መንግስት መመስረትን ጨምሮ ሌሎች መብቶቻቸውን ለማስከበር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የትጥቅ ትግል ያካሄዱ የነበሩት ኢህአዴግና ሌሎች የፖለቲካ ኃይላትም የደርግን መውደቅ ተከትሎ የሚመሰረተው ስርዓት ለዘመናት የኖረውን የማንነትና የስልጣን ባለቤትነት ሕዝባዊ ጥያቄ በመመለስ አገሪቱን ከመበታተን አደጋ የሚታደግ፣ ለመቶዎች ዓመታት በዜጎች ውስጥ የቆየውን  ግጭትና በዚህም ሳቢያ ለተንሰራፋው ድህነትና ኋላ ቀርነት ምንጭ የሆነውን የፖለቲካ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያደርቅ መሆን እንዳለበት ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ችግሩን በአስተማማኝ መልኩ ይቀርፋል ያሉትንም ህገ መንግስት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እንደተደረገው ሳይሆን የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታዎች መሰረት ባደረገና ታይቶ በማይታወቅ ህዝባዊ ተሳትፎና ይሁንታ አፀደቁ፡፡ የህገ መንግስቱን መርህ በመንተራስም ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በእኩል ሁለትነናዊ የመብት ተጠቃሚነትና አገራዊ ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተመሰረተ፡፡

የአገሪቱን የተለያዩ ብሄረሰቦችንና ሕዝቦችን በወከሉ አባላትና አካላት ይህ ስርዓት ሲዋቀር በመፈቃቀድና በመተማመን ላይ የተመሰረተች አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚቻለው በዋናነት በዚህ ዓይነቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አወቃቀር ነው በሚል አሳማኝና ተጨባጭ እሳቤ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በወቅቱ በአንዳንድ የቀድሞዎቹ የአሃዳዊ ስርዓት ደጋፊዎች፣ ጥቂት የውጭ ኃይላትና ምሁራን ዘንድ የተንፀባረቀው አመለካከት ከዚህ እጅግ የተቃረነ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓቱ ኢትዮጵያን ወደመበተን አደጋ ውስጥ ይከታታል የሚል አመለካከትን ነበር ያስተጋቡት፡፡

የኢትዮጵያ አዲሱ የፖለቲካ ስርዓት የተዋቀረበት አግባብ አዲስ ዓይነት መሆኑም በተለይ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብን ትኩረት እንዲስብ አድርጎት ነበር፡፡ አንዳንዶች አድናቆታቸውን ሲቸሩት ሌሎች ግን ምንም ለውጥ አያመጣም ብለው ነበር፡፡ ከእነኝህ የተለዩትም ውጤቱን በቀጣይ አይተው የሚያረጋግጡት ካልሆነ በስተቀር አሁን ላይ ሆነው ይህ ይሆናል ለማለት እንደሚቸገሩ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተለያዩ የዓለም አገራት በተለይም ደግሞ የቀድሞውን አሃዳዊ ስርዓት በሚያመልኩ አንዳንድ የአገሪቱ የፖለቲካ ቡድኖችና ምሁራን ዘንድ የቀረበው ስጋት በዋነኝነት የተመሰረተው በተለይ “የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል” ተብሎ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ላይ የተደነገገው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ አንቀፅ አገሪቱ አንድ ሆና እንዳትቀጥል የሚያደርግና ብዙም ሳይቆይ አገሪቱ ወደመበታተን ማምራቷ የማይቀር መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፁም በወቅቱ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረትና ዩጎዝላቪያ ስር ይተዳደሩ የነበሩትና ራሳቸውን ነፃ አገር ብለው ይፋ ያደረጉትን የተለያዩ አገራት እንደ አብነት በማንሳት ነበር፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያዊያን በዚህ የአንዳንዶች የስጋት ምንጭ ሆኖ በተነገረለት ህገ መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓት ውስጥ ሆነው መኖር ከጀመሩ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ብሔሮችና ሕዝቦች ለዓመታት ሲታገሉለት የኖሩት የማንነት ጥያቄም በተገቢው መልኩ በመመለሱ በባለፉት የ20 ዓመታት ጉዞ ውስጥ መለ የሃገሪቱ ብሄሮች፤ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በፍጹም የመተማመንና የእኩልነት መንፈስ አንድነታቸውን ይበልጥ እያጠናከሩ መጡ እንጂ የተፈራው ስጋት አልደረሰም፤ሃገሪቱም አልተበታተነችም፡፡

የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም አንዳዶች ቅንነት ከተሞላበት ስጋት፤ ሌሎች ደግሞ ከጭርፍን ተቃውሞና ጥላቻ በመነጨ ስሜት ተንብየውት ከነበረው መበታተን ይልቅ ለሌሎች መሰል ችግር ላለባቸው የዓለም አገራት ጭምር ምሳሌ ሊሆን የሚችል መተማመንና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ እኩልነትንና አንድነትን ፈጥረዋል፡፡ ይህ አንድነትም አገሪቱን ለአያሌ ዓመታት ሲያምሳት የኖረውን ግጭት በማስወገድ ሰላምንና ዴሞክራሲን አረጋግጧል፤ በድህነት ውስጥ ሲማቅቁ የነበሩት ዜጎችን ህይወት በእጅጉ ሊቀይር የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ እድገትን እውን የሚያደርግ ጠንካራ መሰረትን ለመጣል አብቅቷል፡፡

ይህ በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ የፖለቲካ ስርዓት የአገሪቱን ሰላምና ብሄራዊ አንድነት ከማጠናከር ባሻገር የህዝቦችን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንና የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነትን አስተማማኝ መሰረት አስይዟል፡፡ በዚህም የተነሳ የአገሪቱ ሕዝቦች ለዘመናት የአገሪቱ መጠሪያ የነበረውን ድህነት በተባበረ ክንዳቸው ታሪክ ለማድረግ በሚያስችላቸው እልህ አስጨራሽ ትግል የህዳሴውን ጉዞ ተያይዘውታል፤የስኬታቸውንም ፍሬ ማየት ጀምረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌደራላዊ ስርዓቱ የፖለቲካ መዋቅር ሥር አብረው የመኖር ፍላጎት ባይኖራቸው ኖሮ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ሰላምና የኢኮኖሚ እድገት በምንም መልኩ ሊታሰብ አይችልም ነበር፡፡

ማሪጅካ ፍራንክ የተባሉ የማህበረሰባዊ ሳይንስ ምሁር ባካሄዱት ጥናት፤ “በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ተግባር ላይ የሚገኘው ፌደራላዊ የፖለቲካ ስርዓት በአገሪቱ ለአያሌ ዓመታት ይስተዋሉ የነበሩትን ግጭቶች አስቀርቷል፤ ይህ ሊሆን የቻለውም በፖለቲካ ስርዓቱ አማካኝነት የተመሰረቱት ክልላዊ መንግስታትና በውስጣቸው የሚገኙት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ፌደራላዊ ስርዓት ስር ሆነው በአንድነት ለመኖር በመፍቀዳቸው ነው፤ ከዚህ አንፃር የፌደራል ስርዓቱ ትልቅ ስኬትን በማሳየት ላይ ይገኛል፤” በማለት በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የፖለቲካ እድገት አረጋግጠዋል፡፡

ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ከሁለት ሳምንታት በፊት በመቀሌ ከተማ  ለተካሄደው ሲምፖዚየም ባቀረቡት ጥናት ላይ የጠቀሷቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካና ታሪክ ተመራማሪ ክርስቶፈር ክላፕ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለተገነባው ውጤታማ ስርዓት ምክንያት የሆነውን ሁኔታ በማንሳት ሲናገሩ፤ “እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1991 የኢትዮጵያው ወታደራዊ ሥርዓት ከስልጣን መወገድ ያስከተለው ውጤት ከአንድ መንግስት መፍረስ በላይ ነው፤ ይህ ወቅት በፈረንጆቹ 1889 አፄ ምኒሊክ ከነገሱበት ጊዜ ጀምሮ ሸዋን ምሰሶ ያደረገ ዘመናዊና የተማከለ ሥርዓተ መንግስት ለመመስረት የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ የተረጋገጠበት ጊዜ ነው፤”  ብለዋል፡፡ የእኚህ ምሁር ይህ ምልከታ የሚያረጋግጠው እውነት ከመቶ ዓመታት በላይ የቆየውን የኢትዮጵያዊያን የእርስ በእርስ መናቆር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገቢ መፍትሄ ማበጀት ያስቻለው ሥርዓት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተዘረጋው የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡

በተጨባጭ የሚታየው እውነት ይህ ሆኖ ሳለ ግን አሁንም አንዳንድ ጨለምተኛ አመለካከት የተጣባቸው አንዳንድ የአገሪቱ የፖለቲካ ተቃዋሚ ኃይላት የሕገ መንግስቱን ሕዝባዊነት በመቃወምና በማውገዝ አቋማቸው ቀጥለውበታል፡፡

በቅርቡ መቀሌ የተከበረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች 6ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ታላቅ ሲምፖዚየም ላይ በህገ መንግስቱ ዙሪያ ጥናት እንዲያቀርቡ ተጋብዘውና ጊዜ ተይዞላቸው ያልተገኙት የኢዴፓው ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ ሰሞኑን ለአንድ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት “የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢህአዴግ አጀንዳ ነው” በማለት ያለምንም ህፍረት መናገራቸው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚከታተሉና እውነቱን በደንብ በሚያውቁት አካላት ዘንድ ትዝብትን እንደሚፈጥር እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡

ምክንያቱም እኚህ ሰው ጥልቅ ለሆነ የፖለቲካ ክርክር (political discourse) እጅግ ተመራጭ የሆነውን መድረክ በመሸሽ የፖለቲካ ጥቅምን ብቻ በማሰብ ያቀረቡት ይህ መናኛ አቋም በምንም ዓይነት ጥናት ያልተደገፈ፤ ቅንጣት እውነትነት የሌለውና ከነባራዊው የአገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ጋር ፍፁም የሚቃረን ቅጥፈት መሆኑ ኢትዮጵያን በቅርብ ለሚያውቋት ሁሉና የእስካሁኑን ጉዞአችንን ሚዛናዊ ሆነው አለያም ገለልተኞች ሆነው ለታዘቡ በይበልጥም ለእኛ ለዜጎቿ  ግልፅ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በህገ መንግስቱና በፌደራል ስርዓቱ ላይ የሚጋረጡ ማናቸውንም ዓይነት አደጋዎች ለመከላከል ዘብ የቆመ ማህበረሰብ ጭምር መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህም ባለፉት ሁለት ምርጫዎች በተለይም በ2002ቱ አገር አቀፍ ምርጫ በተጨባጭ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ የአገሪቱን የመንግስት ስልጣን በመያዝ በስራ ላይ የሚገኘውን ህገ መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓት በሌላ ስርዓት ለመተካት ያለ የሌለ አቅማቸውን ሁሉ ተጠቅመው በእነዚህ ምርጫዎች ላይ ለተካፈሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መራጩ የሰጠው ምላሽ ሕዝቡ ለህገ መንግስቱና ለፌደራላዊው የፖለቲካ ስርዓቱ ያለውን ፍፁም የሆነ ድጋፍ ፍንትው አድርጎ ለማሳየት የሚያስችል በቂ ምስክር ነው፡፡

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ምሁር ማሪጅካ ፍራንክ ጥናትም ህዝቡ ለህገ መንግስቱና ፌደራላዊ ስርዓቱ ቀጣይነት ያለውን ይህንኑ ፅኑ አቋም የበለጠ የሚያጠናክር ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ፣ ሐይማኖትና ባህል ባለቤት የሆኑት የአገሪቱ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ የፖለቲካ ስርዓት ጥላ ስር ሆነው አንድነታቸውን ማጠናከር የቻሉት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ጨምሮ በህገ መንግስቱ ላይ የተረጋገጡትን የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብት ድንጋጌዎችን በአግባቡ ለማስተግበርና ለማስከበር ቁርጠኛ የሆኑ የፖለቲካ መሪዎች የአገሪቱን ስልጣን ይዘው በመቆየታቸው ጭምር ነው፡፡

በመቀሌ ከተማ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን 6ኛ ዓመት በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ በቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች በኢትዮጵያ ጠንካራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት የተቻለው የአገሪቱ ህገ መንግስትና ይህንንም ተከትሎ የተመሰረተው ፌደራላዊ ስርዓት ገና ከጅምሩ ሕዝባዊነትና ብሄራዊ የመፈቃቀድ ባህሪያትን የተላበሰ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ እንደተመለከተው ህገ መንግስቱ እንደሌሎቹ የአገሪቱ ህገ መንግስቶችና የአፍሪካ አገራት ከሌላ የተለየ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ፀባይ ካላቸው ባእድ አገራት ሳይቀዳ አገር በቀል ችግሮችንና መፍትሄዎችን መሰረት በማድረግ የተመሰረተና ሃገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በሚገባ ያገናዘበ መሆኑ በአሁኑ ወቅት ለሚስተዋለው አገራዊ ለውጥ በአወንታዊ መልኩ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

የኢዴፓው አቶ ሙሼን ጨምሮ ህገ መንግስቱንና የፖለቲካ ስርዓቱን የሚቃወሙ አካላት ከዚህ የኢትዮጵያ ያለፉት 20 ዓመታት ተጨባጭ የፖለቲካ ሂደት መማር ከተሳናቸውና ያፈጀና ያረጀ የድሮ አስተሳሰብን ብቻ የሙጥኝ ብሎ ሌት ተቀን በቅዠት መዋተታቸውን እንዲሁ ከገፉበት ምን መምከር ይቻላል? ብሎ ከመጠየቅ ውጭ ሌላ ቃል የለኝም፡፡