የተላላኪዎች ባዶ ጩኸት …

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ እነሆ አምስተኛ ዓመቱን አሳልፏል።  ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት  የግንባታ ሂደት በተያዘለት እቅድ መሠረት እየተከናወነ ይገኛል።

 

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ሂደት ዙሪያ አሁንም ድረስ አልፎ…አልፎ አሉታዊ አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡ በዚህ ዙሪያም በዛሬው  ጽሁፌ የተወሰኑ ነጥቦችን አነሳለሁ።

 

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢፌዴሪ መንግሥት የአባይ ወንዝ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግና ለቀጣናው ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚበጅ እንደሆነ የጠራ አቋም መያዙ ይታወቃል፡፡ ይህን በተመለከተም የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ በተለያዩ ጊዜያት እውነታውን የሚያስረግጡና የሚስረዱ ፅሁፎችን አስነብቧል፡፡

 

በተለይም በመጀመሪያው የግድቡ ግንባታ ምዕራፍ ግብፆች በግድቡ ዙሪያ የሚያሰሙትን አሉታዊ ድምጽ የሚመክት ሚዛናዊ የአፀፋ ፅሁፍ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ ሳቀርብ ቆይቻለሁ።

 

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጉልህ መገለጫ ለሆኑት ነጥቦች ያለኝን ድጋፍ በማያሻማ ልበ ሙሉነት ከማስገንዘብ የቦዘንኩበት አንድም አጋጣሚ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የውኃ ሃብቷ ትርጉም ያለው ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም የሚሰጣትን የልማት ተግባር ለማከናወን ስትነሳ ቁልፍ ጉዳዮችን ታሳቢ አድርጋለች፡፡

 

በመሆኑም ፕሮጀክቱ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት የሚጠቅምና ከዚህ ቀደም በቀጣናው ሰፍኖ የቆየውን የሥጋት መንፈስ የሚያስቀርና መተማመን የሚፈጠር መሆኑን አስረድታለች፡፡ ግልጽነትን የተከተለና የፍትኃዊነት መርህ ላይ ተመስርቶ የሚገነባ መሆኑም ተሰምሮበታል፡፡ ይህን እውነታ ለማስረገጥም ኢትዮጵያ ተገቢው ጥናት እንዲካሄድ አድርጋለች፡፡ በጨለምተኛ አስተሳሰብና አመለካከት ግን የልማት ጉዞው እንደማይገታም አቋም ይዛለች፡፡

 

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ፍትኃዊነትን መሠረት ያደረገ መርህን በመከተል ረገድ የፀና እምነት አላቸው፡፡ አካሄዱ የተፋሰሱ ሀገራት ከሀብቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ የተከተለ ነው፡፡ የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት እንስሳዊ ብሂል ኢትዮጵያ እንደማትከተል ሁሉም ያውቀዋል፡፡

 

አንዳንድ ተጨባጩን እውነታ አምነው መቀበል ያቃታቸው አካላት አሁንም ከየራሳቸው ምኞት በሚመነጭ መሠረተ ቢስ ወሬ እያምታቱ ይገኛል፡፡ በዚህም አንዳች አላስፈላጊ የአመለካከት ብዥታ ለመፍጠር ሲሞክሩ እየታዘብን ነው፡፡ ከዚህ የሰርጐ ገብ ድምጾች እኩይ ሴራ በስተጀርባው እነማን እየዶለቱ እንደሆነ መገንዘቡ ከባድ አይደለም፡፡

 

አሁን በቀጥታ ወደዛሬው መጣጥፌ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ እንለፍና ከህዳሴው ግድብ የግንባታ ሂደት ጋር በተያያዘ መልኩ አሉታዊ እንደምታ ያለውን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ለማዛመት ያለመ መሠረተ ቢስ ወሬ ሲያናፍሱ የምንሰማቸው ፀረ ልማት ኃይሎች እነማን እንደሆኑ እንመለከታለን፡፡

 

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የግርጌ ሀገራት ስንል ሱዳንንና ግብጽን ማለታችን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ሀገራት በግድቡ ዙሪያ አላስፈላጊ አሉባልታን በማይጋብዝ የግልጽነት መንፈስ የሚካሄድ የሦስትዮሽ ውይይት ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል። ሀገራቱም የሦስትዮሽ ውይይቱን ጤናማ የመግባባት መንፈስ በተላበሰ መደማመጥ እያስቀጠሉት ይገኛሉ፡፡

 

ስለሆነም የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን መንግሥታት ይህን ለቀጣናው ህዝቦች ዘለቄታዊ ሠላምና መረጋጋት ፅኑ መሠረት እንደሚጥል የሚታመንበትን ውይይት ማስቀጠሉን ትተው አላስፈላጊ ውዥንብር ይፈጥራሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደኔ የግል ምልከታ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የሚናፈሱ ሰርጐ ገብ ድምጾችን ይጋራሉ ለማለት የሚያስደፍር ነባራዊ እውነታ የለም ባይ ነኝ፡፡

 

ይህ ማለት ግን አገራቱ በውይይት መድረክ ወደ መስማማት መድረሳቸውን የማይወዱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ከሁሉም ወገን ሊኖሩ እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ በሦስቱ ሀገራት የተቋቋመው የሦስትዮሽ የምክክር መድረክ በጤናማ የመተማመን መንፈስ ተጉዞ ከወጫፍ ደርሷል። የግድቡ ግንባታ ሂደትም እየተፋጠነ አሁን አጠቃላይ ግንባታው ከግማሽ በመቶ በላይ ደርሷል፡፡

 

ሰርጐ ገብ የሚለው የአማርኛ ቃል ምንን እንደሚያመላክት ማብራራት የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም፡፡ ሰርጐ ገብ ለተለየ ድብቅ ዓላማ ስኬት የሚንቀሳቀስ የእኩይ ድርጊት ተዋናይ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰርጐ ገብ ድምጾች ስንል ከዚህ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡

 

በተለይም ደግሞ ምንጩ ያልታወቀ ወሬ የማናፈስ አባዜ ለተጠናወታቸው የማህበራዊ ድረገፅ ፖለቲከኞች እና አንዳንድ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን አስነዋሪ ውዥንብር የሚስማማ አገላለጽ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ለማንኛውም ግን ዛሬም በህዳሴው ግድብ የግንባታ ሂደት ዙሪያ አሳቻ አጋጣሚ እየጠበቁ የሚወረወሩ ሰርጐ ገብ ድምጾች ስለመኖራቸው መታዘባችንን ትረዱልኝ ዘንድ እጠቁማለሁ፡፡

 

አንዳንድ የካይሮ መገናኛ ብዙኃንና ምሁራን ያልተፃፈውን እንደማንበብ የሚቆጠር መሠረተ ቢስ ዜና ይዘው ለመውጣት ሞክረዋል፡፡ ይህም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያልተጠበቀ ብዥታን መፍጠሩ አይካድም፡፡ ውሎም ሳያድር ግን እውነታው በመታወቁ የብዠታው ዕድሜ ያጥራል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ።

 

መሠረተ ቢሱ ወሬ ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በተወሰነ ሜጋ ዋት እንድትቀንስ ግብጽ ቀደም ሲል ያቀረበችውን መደራደሪያ ሃሳብ መቀበሏን ያትታል፡፡ ይህንንም በባለሙያዎቹ የምክክር መድረክ ላይ እንዳሳወቀች የመጠቆም ይዘት ነበረው፡፡ ያኔም ቢሆን ይህንን አጀንዳ በመቀስቀስ አቧራ ለማስነሳት ተሞክሯል፡፡

 

ያኔም ቢሆን በዚህ ዙሪያ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ወቅታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ በሀሰት ዘገባዎች የተጠመዱ አንዳንድ የግብፅ መናኛ ብዙኃን ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መሠረተ ቢስ ዜናዎችን ለማሰራጨት ሞክረዋል፡፡

 

ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ከጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ዘገባ ተገቢነትም ተቀባይነትም የለውም፡፡ ነባራዊ እውነታውን በሀሰት በመሸፈን ለማምታታት መሞከርም ውጤቱ ባዶ ነው የሚሆነው፡፡ ትዝብትንም ጥሎ ያልፋል፡፡

 

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከእውነታው የራቀ ዘገባ በማቅረብ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል እየሰፈነ የመጣውን እርስ በርስ የመተማመንና የመደማመጥ መንፈስ ለማደፍረስ የሚደረው ጥረት መቆም አለበት፡፡

 

በመሆኑም እነዚህ መገናኛ ብዙኃን በትክክለኛው ጎዳና ሊጓዙ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የግብፅ መንግሥትም ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ የግድቡ ግንባታ በሦስትዮሽ የጋራ ምክክርና መግባባት እየተከናወነ መሆኑን ሊረዱትና ሊያውቁት ይገባል፡፡ በተለይም አንዳንድ የግብፅ መገኛኛ ብዙኃን ከእውነታው የራቀ ዜናዎችን በማሰራጨት ብዥታ ለመፍጠር መሞከራቸውን ጠቁሜያለሁ። የኦነግ አመራሮችም በተለይ የራሱን የቤት ሥራ መወጣት ለተሳነው ሻዕቢያ መራሹ የኤርትራ መንግሥት ተላላኪ ሆኖ እሪታውን ለማቅለጥ ዳር ዳር እያለ ነው። ባዶ ጩኸት።