ካቢኔው በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ማተኮር አለበት!

                                               
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሀገሪቱ ዕድገት ጋር ይመጥናል ያሉትን 30 አባላት ያሉትን ካቢኔ በአዲስ መልክ አዋቅረዋል። የካቢኔው አወቃቀር ብቃትን፣ ክህሎትንና ውጤታማነትን በመስፈርትነት የያዘ በመሆኑ ተሿሚዎቹ ለተመደቡበት ቦታ ብቁ መሆናቸው የሚያጠራጥር አይመስለኝም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ በምሁራን የተሞላ ካቢኔ የሚያከናውናቸው ጉዳዩች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስለሚሆን፤ የተሻለ ስራ ለማከናወንና ቀደም ሲል በሀገሪቱ ውስጥ ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከማስቻል ረገድ ሚናው ከፍተኛ ይመስለኛል።   
እናም አዲሱ ካቢኔ የሀገሪቱን ችግር በመፍታት ረገድ ፋና ወጊ ሆኖ ይንቀሳቀሳል ተብሎ ይገመታል። በተለይም ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ፋና ወጊ ሆኖና እስከታችኛው የስራ እርከን  ደረጃ ድረስ ወርዶ መስራትና ማሰራት የሚጠበቅበት ይመስለኛል። እርግጥ ብዙውን ጊዜ ሲባል እንደምንሰማው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የሂደት እንጂ የአንድ ጀንበር ክዋኔ አይደለም። ይህ ትክክል ነው። ትግበራው ካለፉት ስርዓቶች ጀምሮ በማህበረሰቡ ውስጥ ሲንከባለሉ የመጡ የተሳሳቱ እሳቤዎችን ጭምር ማረቅ የሚጠይቅ በመሆኑ ጭምር ዘለግ ያለ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።
እንደ እውነቱ ከሆነ መልካም አስተዳደርን በአንድ ጀንበር ለማስፈፀም መሞከር፤ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” እንደሚባለው የአንድ ጊዜ ሆይ…ሆይታ ከመሆን ሊያልፍ የሚችል አይመስለኝም። እናም በሂደትና በሰከነ መንገድ ተግባሩን ማከናወን የግድ ይላል። በሌላ በኩልም ‘መልካም አስተዳደር ጊዜን የሚወስድ ተግባር ነው’ በሚል እሳቤ እጅና እግርን አጣጥፎ መቀመጥ አገባም። ትግበራውን እውን ለማድረግ ቀደም ሲል የተከናወኑ ጉዳዩችን ማጠናከርና የህዝቡን እርካታ ሊፈጥር የሚችል ተደማሪ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። ለዚህም አዲሱ ካቢኔ ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ከወዲሁ ራሱን ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። እርግጥ የመልካም አስተዳደር ትግበራ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕለታዊ ህይወት በቀጥታ የሚነካ ነው። 
ምንም እንኳን በአተገባበሩ ዙሪያ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ መጠነ ሰፊ ተግባራዊ ክንዋኔዎች ቢደረጉም፤ የሚፈለገውን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ግን አልተቻለም። ታዲያ እዚህ ላይ ባለፉት ጊዜያት ምንም ነገር ስላልተከናወነ ሁሉም ነገር ዛሬ ላይ ለአዲሱ ካቢኔ የተተወ ነው እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ምክንያቱም ላለፉት 25 ዓመታት ይብዛም ይነስ ተግባሩን እውን ለማድረግ ጥሩ ጅማሮዎች ያሉት ድርጊቶች ተፈፃሚ ስለሆኑ ነው—የህዝብን እርካታ መፍጠር ባይችሉም።
የኢፌዴሪ መንግስት ባለፉት 25 የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት ውስጥ መልካም አስተዳደር አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት መሆኑን በመገንዘብ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ሊያሰፍኑ የሚችሉ ተቋማትን ከመመስረት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚዎችን አቅም በማጎልበት በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። 
ያም ሆኖ እነዚህ ተግባራት የህዝቡን እርካታና አመኔታ ሊያተርፉ ባለመቻላቸው መንግስት በየደረጃው በአስፈፃሚዎቹ ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ከመውሰድ አልቦዘነም። በጥናት ላይ ከተመሰረተና የችግሩ ምንጭ ምንና የት መሆናቸውን ከማወቅ ባሻገር፣ በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ አስተማሪ ርምጃዎችን ወስዷል። ለመልካም አስተዳደር ተፈፃሚነት ማነቆዎች ናቸው የሚባሉትን ችግሮች ሊቀይሩ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ረገድም ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል። እናም ከትናንት ዛሬ የተሻለ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል።
ይሁንና አሁንም ድረስ ቢሆን የህዝቡን እርካታ መፍጠር አልተቻለም። ለዚህ ደግሞ በመንግስት በኩል ሲገለፅ እንደነበረው፣ የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም የማዋል ፍላጎት ገዥውን ድርሻ እንደሚወስድ ነው። በዚህም ሳቢያ ተሿሚዎችና በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚዎች ህዝቡን ከማገልገል ይልቅ ራሳቸው በህዝቡ የመገልገል ስሜትን አዳብረው በመልካም አስተዳደር አፈፃፀም ጉዞ ላይ አሜኬላ ሆነው ቆመዋል። ይህን ጉዳይ በመቅረፍና የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍታት፤ ህዝብ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ አመኔታ ይዞ የተገልጋይነት ስሜቱ ከፍ እንዲልና ፈፃሚው አካልም የህዝቡ ተቀጣሪና አገልጋይ መሆኑን እንዲያውቅ በማድረግ ረገድ ከአዲሱ ካቢኔ ጉልህ ስራዎች ውስጥ አንዱ መሆን ያለበት ይመስለኛል።
እርግጥ በማንኛውም ሀገር ውስጥ መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ስርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ ግልፅ ነው። ምንም እንኳን የሀገራችን ልመታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ቢኖረውም ቅሉ፤ ይህ የመንግስት ቁርጠኝነት ወደ አስፈፃሚው አካል በተለይም ወደ ታችኛው የስልጣን እርከን እየወረደ በሄደ ቁጥር የመሸርሸር ሁኔታ እያጋጠመው ነው። በተለይም በአንዳንድ የታችኛው የስልጣን እርከን ላይ የህዝብ መሆኑ ተዘንግቶ ፈፃሚዎች እንዳሻቸው ህዝቡን ያንገላቱታል። ከአቅም ማነስ በመነጨም ለህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ አይሰጡም። እናም ከመልካም አስተዳደር አኳያ አዲሱ ካቢኔ ወደ ታች ወርዶ ከተቻለ የማስፈፀም አቅምን መገንባት ካልተቻለ ደግሞ በዚህ ረገድ ብቃት የሌላቸውን አስፈፃሚዎችን ብቃት ባላቸውና የአገልጋይነት መንፈስ በውስጣቸው ባደረ አስፈፃሚዎች መተካት የሚጠበቅበት ይመስለኛል። 
ካቢኔው አንዳንደ አስፈፃሚዎች ራሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች ሆነው በየመድረኩ ስለ መልካም አስተዳደር የሚደሰኩሩ አስመሳዩችንም በመለየት የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ አለበት። መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሃሳብና የታይታ ጉዳይ ባለመሆኑ በእንደዚህ ዓይነት አስፈፃሚዎች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል። ለዚህም የስልጣኑ ባለቤት የሆነውን ህዝብ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ማድረግ አለበት። ይህም የመልካም አስተዳደር ጉድለት ያለበት የትኛውም ተቋም ህዝቡ በህገ መንግስቱ የተጎናፀፈውን ስልጣን በአግባቡ እንዲረዳና የእርሱም ተቀጣሪ መሆኑን እንዲገነዘብ ያደርገዋል።
አዲሱ ካቢኔ የጎንዮሽ ሰንሰለቱን በማስፋትም ለህዝቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበትን ማዕቀፍ ማበጀት ያለበት ይመስለኛል። እንደሚታወቀው መንግስት ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ለሆኑት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓይነት ገለልተኛ ተቋማት ከህብረተሰቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በርካታ ናቸው። ከተቋማቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመመስረትና ራሱን ለመከላከል ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት በማዘጋጀት ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን የሚጠበቅበት ይመስለኛል። 
ይህ ሁኔታም ቅሬታዎች በህዝቡ ውስጥ እንዳይጠራቀምና አመኔታን የሚያጎለብት በመሆኑ፣ ችግሮችን በቅንነት ተቀብሎ ከስር ከስር ለመፍታት ያግዛል። እናም ገለልተኛ ተቋማትን በችግር ፈቺነታቸው በመመልከት የሚከሰቱ ችግሮችን ፈጥኖ ማረም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ገለልተኛ አካላቱ ዋነኛ ስራቸው ህዝቡ በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጡለት መሰረታዊ መብቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ስለሆነ ነው። እነዚህ ገለልተኛ አካላት እስካሁን ድረስ በነበራቸው የስራ አፈፃፀም አቅም በፈቀደ መጠን በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት ህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጡ የመጡ ቢሆንም፤ አሁን ደግሞ አዲሱ ካቢኔ ለሚያከናውኑት ስራ በተጠያቂነት መንፈስ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ከሆነ ተግባራቸውን በላቀ ደረጃ ሊፈፅሙ ይችላሉ። 
ችግሮች እንዳይከማቹና በህዝቡ ውስጥ የቅሬታ መነሻ እንዳይሆኑም ካቢኔው ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል። እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝብን ማዕከል ያደረጉ፣ የተሟሉና ሊያስሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አሉ። ችግሩ እነዚህን የህዝብ ተጠቃሚነት ማዕቀፎች መተግበሩ ላይ ነው። አንዳንዱ ችግር ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ባለማስፈፀም ጭምር የሚገለፅ ነው። ቀላል የማይባሉ ተሿሚዎችና አስፈፃሚዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለህዝቡ በመስጠት ከመስራት ይልቅ፣ ቀደም ሲል መንግሰትም ጭምር እንደገለፀው በራሳቸው ተጠቃሚነት ዙሪያ ይሯሯጣሉ። ህዝቡ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ የመረጠው ፓርቲው ባቀረባቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ አመኔታን ጥሎ ነው። 
ዳሩ ግን አስፈፃሚዎቹ ከገዥው ፓርቲና ከመንግስት ፍላጎትና እምነት ውጪ በመሆን ያልተገባ ተግባር ላይ (በሙስና ተግባራት ላይ በመሳተፍ ጭምር) ህዝቡን ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ እያንዳንዱን ጉዳዩች በመመልከት ረገድ ምንም ነገር በማያመልጠው ህዝብ ዕይታ ውስጥ ይገባና የቅሬታ ሁነኛ መነሾ ይሆናል። እናም ይህን መሰሉን ችግሮች ለመቅረፍ አዲሱ ካቢኔ ማናቸውም ጉዳዩች ተለይቶ በሚታወቅ አሰራሮች እንዲፈፀሙና ቀዳዳዎችን በሚዘጉ መልኩ ገቢራዊ እንዲሆኑ መትጋት ይኖርበታል እላለሁ። ይህም በአሁኑ ወቅት የመልካም አስተዳደር ጉዳይን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት በመደረግ ላይ ያለውን ህዝባዊና መንግስታዊ ጥረት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል። እናም አዲሱ ካቢኔ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ጥርሱን ነክሶ በመስራት የተጣለበትን ህዝባዊ አደራ በብቃት መወጣት አለበት እላለሁ።