አንዳንድ ነጥቦች ስለ ህገ-መንግስቱ “ምሶሶዎች”

                                                                 
ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፓርላማ ቀርበው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጎልበት ረገድ በመንግስት የተያዙ ውጥኖችን የሚዳስሱ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። በተለይም ሀገሪቱ ከምትከተለው የምርጫ ስርዓት አኳያ በፓርላማው የህዝቦችን የተሻለና ተመጣጣኝ ውክልና ለማምጣት፣ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን የመተግበር አስፈላጊነት ውሳኔ መወሰኑንም ገልፀዋል። ለዚህም በህጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን፣ ሀገሪቱ መከተል በሚገባት የምርጫ ስርዓት ዙሪያ ድርድር እንደሚኖርና በድርድሩ የሚገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግም ህጎችን የማሻሻልና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የህገ- መንግስት ማሻሻያዎችን በመቀበል የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ስራ እንደሚሰራም ማስረዳታቸው አይዘነጋም።   
ይሁንና ከሀገራችን የምርጫ ስርዓት ጋር ተያይዞ የገለፁት ህገ-መንግስትን የማሻሻል ጉዳይን አስመልክተው አንዳንድ የተቃውሞው ጎራ አባላት በተሳሳተ መንገድ እየተረዱት በመሆኑ፤ እኔም የበኩሌን ለማለት ብዕሬን ማንሳት ግድ ብሎኛል። በፅንፈኛውም ይሁን ሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ተወዳድረን ስልጣን እንይዛለን በሚሉት አንዳንድ የተቃውሞው ጎራ አመራሮችና አባላት ዘንድ እየተነሳ ያለው ነገር፤ የህገ-መንግስቱ “ምሶሶዎች” (Pillars of the Constitution) ጭምር እንደሚሻሻሉ አድርጎ የመውሰድ ዝንባሌ ነው። 
እርግጥ ይህ እሳቤ አግባብነት ያለው አይመስለኝም። ትክክልም አይደለም። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንድ ህገ-መንግስታዊ ሃሳብ እንዴት ተደርጎ እንደሚሻሻል በግልፅ የሚከተላቸው አሰራሮች አሉ። ያም ሆኖ የህገ-መንግስቱን “ምሶሶዎች” ማሻሻል ማለት ህገ-መንግስቱ የቆመበትን የማዕዘን ድንጋይ የሚቀይርና ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን መሰረት የሚያሳጣ በመሆኑ እነርሱን ማሻሻል ህገ-መንግስቱን ቀዳድዶ የመተው ያህል ይመስለኛል። እናም እነዚህን “ምሶሶዎች” ማሻሻል የሚቻል አይመስለኝም። 
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ወደ ኋላ ላይ የምመለስበት ቢሆንም፤ በመጀመሪያ በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተቀመጡትን የህገ-መንግስት ማሻሻል ድንጋጌዎችን መመልከት ይገባል። እርግጥ እዚህ ላይ “ስለ ህገ-መንግስቱ መሻሻል” ሳወሳ፤ እየገለፅኩ ያለሁት ነገር በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 104 እና 105 ላይ የተገለፁትን ፍሬ ነገሮች መሆኑን አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ እሻለሁ። በህገ-መንግስት አንቀፅ 104 ላይ የሚገኘውና “የህገ-መንግስት ማሻሻያ ሃሳብን ስለማመንጨት” በሚለው ርዕስ ስር፤ የማሻሻያ ሃሳቡን የህዝብና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲደግፉት እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሶስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የደገፉት ከሆነ፤ የማሻሻያ ሃሳቡ ለመላው ህዝብና የህገ- መንግስቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች እንደሚቀርብ ይገልፃል። 
ከዚህ ጎን ለጎንም “ህገ-መንግስቱን ስለማሻሻል” በሚያወሳው አንቀፅ 105 ስር፤ ህገ- መንግስቱን የማሻሻል ጉዳይ ንዑስ አንቀፅ አንድ እስከ ንዑስ አንቀፅ ሁለት ድረስ ባሉት የድንጋጌ ማዕቀፎች ውስጥ ብቻ እንደሚከናወን ተብራርቷል። በዚህ መሰረትም በአንቀፅ 105 (1) ላይ፤ በህገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች በሙሉ፣ ይህ አንቀፅና አንቀፅ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት፤ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት፣ የፌዴራሉ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የቀረበውን ማሻሻያ በሁለት ሶስተኛ ሲፀድቀውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲፀድቀው ብቻ እንደሚሆን ተደንግጓል። 
በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ ሁለት ላይም፤ ከላይ የጠቀስኩት የአንቀፁ ንዑስ አንቀፅ አንድ ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የህገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት፦ (ሀ) የህዝብ ተወካዩችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባቸው የቀረበውን ማሻሻያ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲያጸድቁት እና (ለ) ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሶስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት ብቻ እንደሆነ በግልፅ ተደንግጓል። እነዚህ ህገ-መንግስቱን ስለማሻሻል የሚያወሱት አንቀፆች የህገ-መንግስቱ ዴሞክራሲያዊነት ትክክለኛ መገለጫዎች ይመስሉኛል። ለዚህም ይመስለኛል— ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “…አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የህገ- መንግስት ማሻሻያዎችን በመቀበል የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ስራ ይሰራል” በማለት በቅርቡ ለፓርላማ የገለፁት። ይህ ማለት ግን ህገ-መንግስቱ የተመሰረተባቸውን የማዕዘን ድንጋዩች ይቀየራሉ ማለት አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል።   
እርግጥ የህገ- መንግስቱ ባለቤት ገዥው ፓርቲ አይደለም። ‘ለምን?’ ቢባል፤ ዋነኛው ባለቤቱ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸውና። ለዚህም ህገ- መንግስቱ በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጱያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች… በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት…ህገ- መንግስቱን በተወካዮቻችን አማካኝነት አፅድቀነዋል” የሚለውን አባባል መጥቀስ የሚቻለ ይመስለኛል። 
ለነገሩ እዚህ ላይ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አሁን በስራ ላይ ላለው ህገ- መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት እውን መሆን መታገሉ፤ ማታገሉና በሂደቱም መስዋዕትነት መክፈሉ የሚካድ አይደለም። በዚህም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከአምባገነኑ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአፈና አገዛዝ አላቋል። በሀገራችን የፀረ- ዴሞክራሲ ኢኮኖሚያዊ መሰረትን ንዷል፣ የብሔራዊ ጭቆናን ተቋማዊና መዋቅራዊ እንዲሁም ድርጅታዊና ርእዮተ ዓለማዊ መሰረቶች ከመሰረታቸው እንዲመነገሉ  አድርጓል። 
ከዚህ በተጨማሪ፤ የግልና የቡድን መብቶችን ያጣመረ ዴሞክራሲን መገንባት ችሏል። እነዚህና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት እምነቶች ለህዝብ ቀርበው እስከ ታች ድረስ የወረደ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸው ማሻሻያ ከተደረገባቸው በኋላ፤ በህገ- መንግስትነት እንዲፀድቁና ህዝቡ “የእኔ ናቸው” ብሎ እንዲቀበላቸው አድርጓል። ይህም ዴሞክራሲያዊው ስርዓት እንዲፈጠር ገዥው ፓርቲ የመሪነት ሚናውን በብቃት ቢወጣም፤ በስተመጨረሻም የህገ- መንግስቱ ባለቤት ህዝቡ መሆኑን በግልፅ የሚያስረዳ ዕውነታ ይመስለኛል። 
ይህ ብቻ አይደለም። ለህገ- መንግስቱ መሰረት በሚካሄዱ ምርጫዎች ህዝቡ ድምፅ የሚሰጠው ህገ- መንግስቱን ለሚንከባከብለትና ለሚጠብቀው ኃይል መሆኑ ለአምስት ለተከታታይ የምርጫ ጊዜያት ታይቷል። ይህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አምነውበትና ተስማምተውበት ያፀደቁትን ዴሞክራሲያዊ ህገ- መንግስት የትኛውም ኃይል እንዲነካባቸው የማይፈልጉ መሆኑን የሚያሳይ ሃቅ ነው። 
ለዚህም ፀረ- ህገ- መንግስታዊነትን እያቀነቀኑ ለአምስት ጊዜያት ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ  ተወዳድረው ያገኙትን ውጤት ዛሬም በተቃዋሚነት ጎራ ከሚገኙት ወገኖች ውጪ ማንንም በእማኝነት መጥቀስ የሚቻል አይመስለኝም— ነገሩ “ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” እንዲሉት ዓይነት ነውና። ያም ሆነ ይህ ግን ከህገ- መንግስቱ ውስጥ አንቀፆችን መሰረዝም ይሁን ማሻሻል የሚችሉት የሀገራችን ህዝቦች ወይም ስልጣናቸውን በውክልና በመስጠት የመረጡት አካል እንጂ የትኛውም አካል አለመሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። በእኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትም ከዚሁ መሰረታዊ እምነት የመነጨ እንጂ፣ ከህገ-መንግስቱ “ምሶሶዎች” ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና ያለው አይመስለኝም። ይህ እምነቴም ቀደም ሲል “ኋላ ላይ እመለስባቸዋለሁ” ወዳልኳቸውና “መቀየር የሚችሉ አይመስሉኝም” የሚል ድምዳሜ ወዳሳረፍኩባቸው የህገ-መንግሰቱ “ምሶሶዎች” ይወስደናል። እናም በቅድሚያ ‘ለመሆኑ እነዚህ የህገ-መንግስቱ የማዕዘን ድንጋይ እነማን ናቸው?’ ከሚል ጥያቄ መነሳት ተገቢ ይመስለኛል።
የህገ-መንግስቱ “ምሶሶዎች” ተብለው በመሰረታዊነት ከሚጠቀሱት ውስጥ፤ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የተከበሩበት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት፣ ራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የነፃ ገበያ መርህና በዚሁ ማዕቀፍ የመሬት አስተዳደር  በመንግስትና በህዝብ ስር እንዲሆን ማድረግ የሚሉት ዋነኛዎቹ ናቸው። በእኔ እምነት እነዚህን የህገ-መንግስቱን የማዕዘን ድንጋዩች መቃወም አሊያም ከህገ-መንግስቱ ውስጥ እንዲወጡ ማለም ማለት፤ እንደ አፄው ስርዓት ወቅት “ስዩመ-እግዚሐብሔር” እየተባለ መንግስትና ሃይማኖት አንድ እንዲሆኑ መመኘት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን የሚጨፈልቁት ያለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ተመልሰው እንዲመጡ መሻት፣ የሌሎች ፍላጎቶችን ለማሟላት ሲባል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶችን እንዲታፈኑ መፍቀድ አሊያም ያለፈውን የሶሻሊስት ስርዓትን በመናፈቅ የነፃ ገበያ ስርዓት መርህ እንዳይኖር መፈለግ እንዲሁም የአርሶ አደሩን መሬት በመሸጥና በመለወጥ ጭሰኛ ሆኖ እንዲቀር መፈለግ ማለት ነው። 
ሆኖም በእኔ  እምነት እነዚህን ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ፀረ-ልማታዊ አስተሳሰቦችን ጫንቃው ላይ ጭኖ ለመሸከም የሚፈቅድ ማህበረሰብ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር አይመስለኝም። የለምም። የሀገራችን ህዝቦች እነዚህን ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ልማታዊ እሳቤዎችን አምርሮ የሚጠላቸውና ከጫንቃው ላይም እንዲወገዱ በፅናት የታገላቸው ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ያለፉ ስርዓቶች ተግባራትን ማለም ህገ-መንግስቱን ዕውን ለማድረግ ውድ ህይወቱን ከከፈለው የሀገራችን ህዝብ ጋር አይንና ናጫ መሆን ይመስለኛል። 
ሁላችንም እንደምናውቀው እንደ ኢትዮጵያ ህዝቦች የፀረ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶችን አስከፊነት የሚያውቅ የለም—ከራሳቸው ተጨባጭ ልምድ በሚገባ ይገነዘቡታልና። እናም የህገ-መንግስቱ “ምሶሶዎች” በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ መኖርን በምንም መንገድ ሊፈቅዱት አይችሉም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ባለፉት 22 ህገ-መንግስታዊ ዓመታት የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን በሚገባ ማጣጣማቸው፣ የጀመሩት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያድግላቸውና እንዲመነደግላቸው ይሻሉ እንጂ፤ ዳግም ተመልሰው በኢ-ሰብዓዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ መዳከርን አይመኙም፤ ሊያስቡትም የሚፈልጉ አይመስለኝም። እናም በርካታ መስዕዋትነት የከፈሉበትንና የቃል ኪዳን ሰነዳቸው የሆነውን ህገ-መንግስት እንደ ዓይናቸው ብሌን ይንከባከቡታል።
ህገ-መንግስቱ በራሳቸው የደም ጠብታ የፃፉት የጋራ ሰምምነት ሰነዳቸው በመሆኑም፤ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ባልተገባ ሁኔታ ሊቆርሱት እንዲመኙ ዕድል የሚሰጧቸው አይመስለኝም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ላለፉት 22 ህገ-መንግስታዊ ዓመታት የተጎናፀፉትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳጧቸው መሆኑን ስለሚያውቁም፤ ለሰነቁት ራዕይና የህዳሴ ጉዞ ደንቃራ እንዲሆኑባቸው ይፈቅዳሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል። 
ያም ሆነ ይህ ግን ህገ-መንግስቱን የሚቃወሙ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ማወቅ ያለባቸው ሃቅ ያለ ይመስለኛል—የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነዳቸውን እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚጠብቁት እንጂ፤ “ምሶሶዎቹ” ተነቅለው የሌላ ሀገር ህገ-መንግስት እንዲሆን እንደ ባይተዋር በትዝብት የሚያዩት አይደለም—በደማቸው የዋጁትና የዘመናት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎቻቸውን መመለስ የቻለ ብቸኛ ሀገራዊ ሰነድ ነውና። ለዚህም ነው—የህገ-መንግስቱን “ምሶሶዎች” መናድ ህገ-መንግስቱን መናድ ነው የሚባለው። ስለሆም ስለ ህገ-መንግስቱ “መሻሻል” ጉዳይ ሲነሳ ሶስት ርምጃዎችን በምናብ ምኞት ወደፊት ሄዶ ያልተባለን ነገር ማለም፤ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ከመሆን የሚዘል አይመስለኝም።