ከድህነት የወጣች ብቻ ሳይሆን ሞዴል ሀገር . .

.
                                                                           
ለለውጥ የተጋ ትውልድ ሀገሩን ወደ ላቀ ምእራፍ እንደሚያሸጋግራት በርካታ ሀገራትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የእኛም ሀገር በበቂ ምሳሌነት ልትነሳ ትችላለች፡፡ ተጠቃሽ የሆኑ የልማትና የእድገት ለውጦችን አስመዝግባለች፡፡ የአፍሪካና የእስያ ሀገራት በምሳሌነት እየጠቀሱዋት ይገኛሉ፡፡ ኋላቀር ከሆነ ሀገራዊ ኢኮኖሚ፣ ከከፋ ድህነትና ረሀብ፣ ተመጽዋችነትና ተረጂነት ለመውጣት ያደረገችውና በማድረግም ላይ ያለችው ትግል የሚታዩ፣ የሚጨበጡ፣ ተጠቃሽም የሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃም ምስክርነት የተሰጠባቸውን ለውጦች አስመዝግበዋል፡፡ ጅምሩ ይጎለብት ዘንድ እንተጋለን፡፡ የጥፋት ሀይሎችም ይመከታሉ፤  የሚለው የዚህ ፅሁፍ ማእከላዊ ጭብጥ ነው።
የደረስንበትን ደረጃ ጠብቀን ለላቀ ውጤት መገስገስ የሀገራችንን ሰላም መጠበቅ የማንም ሳይሆን የራሳችን ሀላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በላይ ሊቆም ሊያስብ ሊቆረቆር የሚችል ማንም አይኖርም፡፡ ሀገሪቱ የደረሰችበት እድገት ክፉኛ ያቆሰላቸው የቅርብና የሩቅ ጠላቶችዋ እንደገና ወደነበረችበት እንድትመለስ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሁከት፣ ብጥብጥና ግጭት በህዝቡ ውስጥ እንዲፈጠር ሲሰሩ ኖረዋል፤ ዛሬም አላረፉም፡፡
ይህንን እኩይ ሴራቸውን የማምከን ለሀገርና ለህዝብ ክብርና ሰላም ጸንቶ መቆም የመንግስት ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት የህዝብ ሀላፊነት ነው የሚሆነው፡፡ መንግስታት ይቀያየራሉ፡፡ ይለወጣሉ፡፡ ሀገር ደግሞ አትለወጥም፡፡ ሁለትም ሶስትም አይደለችም፡፡ ሀገር አንድ ብቻ ናት፡፡ በህይወት ዘመኑ አንድ ሰው ሊኖረው የሚችለው ትልቁ ሀብቱና መኩሪያው የተፈጠረባት ሀገሩ ነች፡፡ የሀገሩን ሰላምና እድገት እንጂ ውድቀትዋን አይሻም፤ ማየትም አይፈልግም፡፡
ከትላንትዋ ኢትዮጵያ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በብዙ መስክ የተሻለች፣ የለማች፣ የጎለበተች፣ የዘመነች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በመሰረተ ልማት በብዙ በርካታ መስኮች የተመዘገቡት አመርቂ ውጤቶች የዚህችን ሀገር መጻኢ ብሩህ እድል አመላካች ናቸው፡፡ ታላቅ ተስፋን የሰነቀች ወደ ታላቅነት ምእራፍም እየተሸጋገረች ያለች ሀገር ነች፡፡
ይሄንን እመርታዊ ሀገራዊ ልማትና እድገት ለመግታት ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች በውስጥ ያሉ ተላላኪዎችንና በገንዘብ የገዙዋቸውን ቅጥረኞች በማሰማራት ሀገራዊ ሰላምን የማደፍረስ  ለዛሬውም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ የሚበጁትን የተገነቡትን ስራዎች በማፍረስና በማውደም ተግባር ተጠምደው ሰንብተዋል፡፡
እነዚህ የኦነግና የግብጽ የሻእቢያ የሌሎችም አሸባሪና አክራሪ ሀይሎች ተላላኪዎች ህዝቡን ለማደናገር ጭምብል ለብሰው ተመሳስለው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቢሆንም ማንነታቸው በውል ተለይቶ ስለታወቀ ህዝቡ ከመንግስት ጋር በመሆን የመመንጠርና ለይቶ የማውጣት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ሀገር ለማውደም ለማጥፋት በውጭ ሀይሎች ተገዝተው የተሰማሩ መሆናቸው በመታወቁ ምክንያት ከእንግዲህ የሚደበቁበትም ሆነ የሚሸሸጉበት ዋሻ የላቸውም፡፡ አይኖራቸውም፡፡
በሀገር ውስጥ ህዝቡ የሚያነሳቸው ችግሮች የሚፈቱት በህዝቡና በመንግስት የጋራ ውይይት መግባባትና መነጋገር ነው፡፡ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት አያስፈልገውም፡፡ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትም አይችሉም፡፡ ኦነግ ከግብጽ መንግስት ያገኘውን  ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ በኦሮሚያ አካባቢ በመንዛትና በማሰራጨት በፈጠረው ሁከትና ግጭት  ለንብረት መውድምና ለሰው ህይወት መጥፋት ታላቅ ምክንያት ሆኖአል፡፡ ራሱም የድርጊቱ ፈጻሚና መሪ እኔ ነኝ ሲል ሀላፊነቱን ወስዶአል፡፡
ይህ ወንጀለኛና አሸባሪ ድርጅት ሞቶ ከተቀበረበት በመነሳት ለመንፈራገጥ ቢሞክርም ዛሬም አቅመ ደካማና ለ50 አመታት ራሱን ችሎ ለመቆም ያልበቃ  በተለያዩ አንጃዎች  የተከፋፈለ በመሆኑም ከተላላኪነት ያለፈ ትርጉም ያለው ማንነት እንኳ የለውም፡፡ የግብጽ አላማ አስፈጻሚ ሁኖ በጥፋት ተግባር መሰማራቱ በህዝብና በአባ ገዳዎች ላይ በተግባር ያሳየው ንቀትና ድፍረት ህዝቡን ለአደጋ አጋልጦ በፈጠረው ሁከትና ግርግር የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት ማለፉ በታሪክ ውስጥ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ በወንጀል  በተሞሉ  አረመኔያዊ  ድርጊቶቹም ተጠያቂ የሚሆንበት ግዜ ከቶም ሩቅ አይሆንም፡፡
አላማቸው በውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር መንግስት ተረጋግቶ የተጀመረውን ልማትና እድገት እንዳያስቀጥል የትኩረት አቅጣጫውን ማስቀየር በሰላም እጦት እንዲወጠር ነገ ሀገሪቱን ወደላቀ የእድገት ማማ የሚያስፈነጥሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲዘጉ ለማድረግ በግብጽ እየተረዱ የሚያደርጉት መፍጭርጨር ነው፡፡
አስተባባሪውና በቅርብ ጎረቤት የሆነው የሻእቢያ መንግስት ከግብጽ መንግስት ጋር በመሆን  ዘመን የማይሽረውን ጠላትነቱን ይዞ እነብርሀኑ ነጋን፣ አልሻባብን፣ ኦነግን፣ ኦብነግንና ሌሎችን የብሄረሰብ ድርጅቶችን እያደራጀ፣ እያስታጠቀ በአገኘው አጋጣሚ አስርጎ ለማስገባት እየሞከረ ኢትዮጵያ ተበታትና ተከፋፍላ እንድትኖር በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ቡድኖች እንቅስቃሴና ለኢትዮጵያ ያለው አደጋ ግልጽ ነው፡፡ ልዩነቶቻችንን በልዩነት ይዘን በጋራ ጉዳይ ደግሞ በቅድሚያ ሀገራችንንና ህዝባችንን ከከፋ አደጋ መከላከል የወቅቱ የተቃዋሚውም፣ የህዝብም፣ የመንግስትም የጋራ አጀንዳ መሆን እያለበት እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ አክራሪውና ጽንፈኛው ተቃዋሚ ኦነግ ኦሮሚያን፤ ኦብነግ ኦጋዴንን፤ ሌላው ጋምቤላን፤ ሌላው ሲዳማን፣ እስላማዊ አክራሪው በሸሪአ የሚመራ መንግስት በኢትዮጵያ እመሰርታለሁ በሚል በየፊናቸው እያደረጉ ያሉት ሩጫ ሀገርና ህዝብ ለማጥፋት ያቀደ በመሆኑ ስለሀገር ጸንቶ መቆም ግድ ይላል፡፡ 
መንግስት ከተጋረጠው አደጋ ሀገሪትዋን እየተከላከለ ጠብቆ ለማልማትና ለማሳደግ ረዥም ርቀት ሂዶ ተጨባጭ ስራም ሰርቶአል፡፡አንድነትዋን ለመጠበቅ የሚከፈለውን መስዋእትነት ከፍሎአል፡፡ከጠላቶችዋ ጋር ወግኖ ሊያጠፋት የተዘጋጀው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው አውሮፓና አሜሪካ መሽጎ ሲያውካካ ውሎ የሚያድረው አክራሪ ሀይል ምን እያደረገ እንደሆነ ራሱን ሊጠይቅበት የሚገባው ግዜ አሁን ነው፡፡
አክራሪውና ጽንፈኛው ሀይል የሀገርን ሞትና ውድመት የህዝብንም እልቂትና ጥፋት ደግሶአልና ከህዝቡ የሚሰጣቸው ምላሽ የከፋ ነው፡፡ በተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ የድሀውን ልጅ እሳት ውስጥ ለመማገድ ወሬና አሉባልታ እየነዙ፣ የህዝብን አብሮነት ለማፍረስ፣ ለማባላትና ለማፋጀት እየሮጡ  ለሀገርና ለህዝብ ቆመናል የማለት የሞራል ብቃት  የላቸውም፡፡
በድሀ ልጅ ደምና ሞት የሚነግድ ውጥንቅጡ የወጣ  መንጋ የህዝብ ወገን፣ የህዝብ ልጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለማይችልም ህዝቡ እስከ መጨረሻው ድረስ ሊዋጋው፣ ሊፋለመው የወሰነበት ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡
እርስ በእርስ የማይግባቡ፣ በአንድ መቆም የማይችሉ፣ ተመልሰውም በፉክክር  የሚወነጃጀሉ፣ የሚጠፋፉ ተቃዋሚዎች አንዲትን ታላቅ ሀገርና ህዝብ ለመምራት ብቃቱ የላቸውም፡፡ ስለሀገርና ህዝብ ደንታ የሌላቸው ነገ በሀገር ላይ ምን ሊፈጠር ይችላል ብለው እንኳን  የወደፊቱን መገመት የማይችሉ በጥላቻና በአጉል ባዶ እብሪት የሚናውዙ ተቃዋሚዎች ለሀገር ይበጃሉ ተብሎ አይታመንም፡፡
መሪዎቹን በህግና በስርአት በሰላማዊ ምርጫ ከስልጣን ለማውረድ ይችል የነበረው የአረቡ አለም በእብደት እየጋለበ በየአደባባዩ በተቃውሞ ሰልፍ ሀገር ምድሩን ሲያናውጥ፣ ጎማ ሲያቃጥል፣ ድንጋይ ሲኮለኩል፣ መኪናዎችን ሲያነድ፣ ሙዚየሞችን ሲዘርፍ የገዛ ሀገሩን ሀብት ድርጅትና ኢኮኖሚ ሲያወድም፣ እሳት ሲያነድ ውሎ አድሮ ያገኘው ታላቅ ትርፍ  የታፈረችና የተከበረች ሀገሩን ማጣት፣ ስደትና ሞት ብቻ ነው፡፡
ዛሬ ቢጸጸት ቢያዝን ደም እንባ ቢያለቅስ ውሀ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው የሆነበት፡፡ አክራሪና ጽንፈኛ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች በባዶ ተስፋ እየነዱ የማይወጣበት መቀመቅ ውስጥ ከተቱት፡፡ ሀገሩንና ሰላሙን ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ ሊመልሳቸው አልቻለም፡፡ ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ የሚባለው ተረት በእነሱ ላይ ሰራ፡፡ የማግሬቡ አብዮት ጥፋትና ውድመት እንጂ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ፍትህን አላመጣም፡፡ እኛ የጀመርነውን ታላቅ ሀገር የመገንባት ራእይ ሊያሰናክሉ የሚራወጡትን ሀይሎች በመመከት ጅምራችንን ማጎልበት ይጠበቅብናል፡፡