መከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አሸባሪው ሸኔ ሲጠቀምባቸው የነበሩ 2 ማሰልጠኛዎችን አወደሙ

ጥር 30/2014 (ዋልታ) ከአሸባሪው ትሕነግ ጋር እየተናበበ የሴራ ድሩን የዘረጋው ሸኔ የጥፋት ቡድን አባላቱን ያሰለጥንባቸው የነበሩ 2 ማሰልጠኛዎች እንዲወድሙ መደረጉን የአገር መከላከያና ፌደራል ፖሊስ አስታወቁ።
የምስራቅ ዕዝ አንድ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል አዲሱ መሐመድ እና በፌደራል ፖሊስ የምስራቅ ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን 5 አዛዥ ከማንደር አህመድ ፈዮ ናቸው ይህን የገለፁት።
ሰንቀሌና ቀልቀልቲ የተሰኙት ማሰልጠኛዎችን ማውደም የተቻለው የክፍለ ጦሩ የሠራዊት አባላት ከዲቪዥኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት ጋር በትብብር ባደረጉት የተቀናጀ ዘመቻ ነው ብለዋል።
በማሰልጠኛው ውስጥ በስልጠና ላይ የነበሩትን ጨምሮ ተተኳሾችና የጦር መሳሪያዎች መማረካቸውንም አመራሮቹ ስለመግለፃቸው የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።
የአሸባሪው ትሕነግን ተልዕኮ ለማስፈፀም እየሰሩ ያሉት የሸኔ አባላት ላይ የሚደረገው ምንጠራ ተጠናክሮ መቀጠሉ የተገለፀ ሲሆን በቅርቡ በተደረገ ዘመቻ ከ100 በላይ የአሸባሪው ሸኔ አባላት መደምሰሳቸውንና ከ600 በላይ ደግሞ መማረካቸውን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አህመድ አሊ በበኩላቸው፣ የመከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች አገርን ከብተና ለማዳን በከፈሉት መስዋዕትነት ለተገኘው ሰላም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዞኑ አሸባሪውን ትሕነግን ለመደምሰስ በተደረገው ዘመቻ የሚሊሻ አባላትን በማሰለፍ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለውን ሎጀስቲክሳዊ አቅርቦት ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ማድረጉን ያወሱት ዋና አስተዳዳሪው አሸባሪውን ሸኔን ለመደምሰስም በሚደረገው ዘመቻ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።