ምክር ቤቱ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት የሚያከናውኑትን ሴራ አወገዘ

ኅዳር 7/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግስት ለመመስረት ለሚያደርጉት መፍጨርጨር የሚያጎበድዱ የወገን ባንዳዎች ከክህደት ተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳሰበ፡፡
አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ፌዴራል-ኮንፌደራል ኃይል በሚል አካሄድ በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት የሚያከናውኑትን ሴራም አውግዘዋል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ ፈተናዎችን በድል የተሻገረች፣ ዜጎቿም በሉዓላዊነትና በነፃነት ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱ የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል።
የአሸባሪው ሕወሓት ወራሪ ኃይል በወረራ በፈጸመባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች በርካታ ውድመት ማድረሱም ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለገጠማት ችግር ምንጩ በስልጣን ጥም የሰከረውና ሰብዓዊነት የሌለው አሸባሪው ሕወሓት መሆኑንም ምክር ቤቱ ገልጿል።
የጋራ ምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ አካሉ ለኅልውና ዘመቻው ውጤታማነት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ባሉት መዋቅሮች የሃብት አሰባሳቢ፣ የደህንነትና ጸጥታ እንዲሁም የአደረጃጀት ኮሚቴ በማቋቋም ምክር ቤቱ ወደስራ መግባቱን ገልጸዋል።
ለዚሁ ተፈፃሚነትም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ግንባር በመዝመት፣ ለሰራዊቱ ደጀን በመሆንና የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡