ሴኔጋል ግብፅን 4 ለ 2 አሸንፋ የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች

ጥር 30/2014 (ዋልታ) በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል ግብፅን በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት 4 ለ 2 አሸንፋ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን አነሳች።
በመድረኩ ለ8ኛ ጊዜ ዋንጫ አንስታ በእጇ ያለውን ክብረወሰን የበለጠ የማራቅ እቅድ የነበራት ግብፅ ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል።
120 ደቂቃ ግብ ሳይቆጠር ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ባመራው ጨዋታ የቴራንጋ አንበሶቹ በሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔ እየተመሩ ተጋጣሚያቸውን 4 ለ 2 በመለያ ምት በማሸነፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት መሆን ችለዋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሴኔጋል ፍፁም ቅጣት ምት አግኝታ ሳዲዮ ማኔ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ውድድሩ በሴኔጋል የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ካፍ ኮከቦችን አሳውቋል።
በዚህም ሳዲዮ ማኔ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ሲመረጥ የካሜሮኑ ቪንሰንት አቡበከር በስምንት ግቦች የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ሆኗል።
የሴኔጋሉ ግብ ጠባቂ ቤንጃሚን ሜንዲ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ በሚል ተመርጧል።