በትግራይ 75 በመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ ነው

መጋቢት 06/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል 75 በመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በግማሽ አቅም አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ብሔራዊ ኮሚቴ አስታውቀ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ብሔራዊ ኮሚቴ ሳምንታዊ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

ኮሚቴው በስብሰባው በትግራይ ክልል የአባል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ስራዎች አፈፃፀምን ገምግሟል፡፡

በዚህም በክልሉ ከሚገኙ ሆስፒታሎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ እንዲሁም 10 በመቶ የሚሆኑት በከፊል ስራ መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡

ባለፉት 2 ሳምንታት 1 ሺህ 583 እናቶች በነዚሁ ተቋማት አገልግሎት ማግኘታቸው ተጠቁሞ 967 ተኝቶ ታካሚዎች እና 44 ሺህ ተመላላሽ ታካሚዎች መስተናገዳቸው ተጠቅሷል፡፡

በክልሉ ከሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በስራ ገበታ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

30 ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድኖች በክልሉ እየተዘዋወሩ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ዝግጅት መጠናቀቁ እና ትምህርት ቤቶቹን ስራ ለማስጀመርም ከመምህራን እና ወላጆች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ በቅርቡ ስራ እንዲጀምሩ የተወሰነ መሆኑ እና ይህን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች መሰራጨታቸውም ተጠቁሟል፡፡

በውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ 13 ተቋማት 162 ቦቴ መኪኖችን መድበው በውሃ አቅርቦት ላይ በቅንጅት እየሰሩ ነው ተብሏል፡፡

አብዛኛው የክልሉ መደበኛ ፖሊስ የስራ ኃላፊዎች እና አባላት በስራ ላይ መሆናቸው እና ፖሊስ ጣቢያዎችም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ  አመላክቷል፡፡

በመቐለም ፍርድ ቤት ስራ መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን  በቀጣይ ዜጎችን በቋሚነት መልሶ የማቋቋምና ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ የሚያስችል ስራ ለመስራት ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው፡፡