በጎርጎራ ፕሮጀክት ለመሰማራት 120 ባለሃብቶች ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለፀ

 

የ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክትን ተከትሎ 120 ባለሃብቶች በጎርጎራ ከተማ በተለያየ የልማት ዘርፍ ለመሰማራት የፕሮጀክት ንድፈ ሀሳብ ማስገባታቸውን የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ አስታወቀ።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ አይቼው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በጎርጎራ የ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት መጀመሩን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ባለሀብት በአካባቢው የልማት ቦታ እየጠየቀ ነው። ወረዳውም ለዚህ የሚሆኑ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል።

ባለሀብቶቹ በሎጅ፣ በሆቴልና ሪዞርት ልማት ላይ ለመሳተፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን የጠቆሙት አስተዳዳሪው፣ የተቀሩት ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ማቀነባበሪያ፣ በዓሣ እርባታ፣ በእንስሳት በተለይ በዶሮ እርባታ፣ በአኩሪ አተር ልማት፣ በከሰል ድንጋይ ልማት ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን አስታውቀዋል።

በእንስሳት መኖ ማልማትና ማቀነባበርን እንዲሁም በንብ ማነብ ለመሳተፍ ፍላጎቶች ከባለሀብቶች በኩል መምጣቱንም ተናግረዋል።

እንደ ወረዳ አስተዳዳሪው ገለፃ፤ አካባቢው ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በልማት ለመሰማራት ፍላጎት ላሳዩ ባለሀብቶች ቦታ የተሰጠ ቢሆንም በጊዜው የነበረው ክትትል ደካማ በመሆኑ ባለሀብቶቹ በቀረጿቸው ፕሮጀክቶች መሰረት ማልማት ባለመቻላቸው መሬታቸው ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን አስታውቀዋል።

ጎርጎራ ለልማት ምቹ የሆነች ቦታ ብትሆንም ከዚህ በፊት ከልማት የተገለለች ከተማ ናት፤ በዚህም መሰረት የአካባቢው ህብረተሰብ የመልማት ጥያቄ ሲያነሳ ነበር፤ ይህ አጋጣሚ ሲመጣ ሕዝቡ ከምንም በላይ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶታል ያሉት አስተዳዳሪ፣ የጎርጎራ ማደግ ለአካባቢውና ለጎንደር ከተማ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃትን የሚፈጥር በመሆኑ ሕዝቡ በጉጉት እየተጠባበቀው ነውም ብለዋል።