ከተማ አስተዳደሩ ለቦረና ዞን የድርቅ ተጎጂዎች ያዘጋጀውን ድጋፍ ወደ ስፍራው ላከ

የካቲት 21/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቦረና ዞን የድርቅ ተጎጂዎች ከተለያዩ ተቋማት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰበውን ድጋፍ ዛሬ ማለዳ ወደ ስፍራው ላከ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ድጋፉን አስረክበዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት ድጋፉ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት እና የህብረተሰብ ክፍሎች መሰባሰቡን ተናግረዋል።

ድጋፉ 250 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ሁለተኛ ዙር እንደሚደረግም አመላክተዋል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ በዞኑ የተከሰተው ድርቅ በተከታታይ በክልሉ 10 ዞኖች ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዛሬው እለት በተደረገው ድጋፍ የምግብ፣ የእንስሳት መኖ፣ የውሃ ቦቴዎች እንደሚገኙበትም የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ድርቅ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንደሚሹ ክልሉ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።