የሞርካ-ግርጫ-ጨንቻ የመንገድ ፕሮጀክት ላይ የሚታየው መዘግየት በአፋጣኝ መፈታት አለበት – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

የካቲት 20/2013 (ዋልታ) – የሞርካ -ግርጫ-ጨንቻ የመንገድ ፕሮጀክት ላይ የሚታየው መዘግየት በአፋጣኝ መፈታት እንዳለበት የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሳስበዋል፡፡

ዋና አፈ ጉባኤውና የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የደቡብ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዲሁም የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች የፕሮጀክቱን አፈፃፀም በተመለከተ ከግንባታው ፈፃሚ አካላት ጋር የመስክ ምልከታና ውይይት አድርገዋል።

ወደ 2 ቢሊየን ብር በሆነ ወጪ የሚገነባው የሞርካ-ግርጫ-ጨንቻ መንገድ 72 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው።

ቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ በተሰኘ ተቋራጭ ግንባታው የሚያከናውን ሲሆን ግንባታው በ2011 ዓ.ም ነው የተጀመረው፡፡
በቀጣዩ አመት እንደሚጠናቀቅ እቅድ የተያዘለት ቢሆንም የእስካሁኑ የግንባታው አፈፃፀም 15% ብቻ ነው።

የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሃንዲስ አስቻለው ባልቻ ለፕሮጀክቱ መጓተት የዲዛይን ለውጥ፣ አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ፣ የወሰን ማስከበር ስራ በተያዘለት ጊዜ አለመፈፀሙ እና መሰል ተግዳሮቶች ምክንያት ናቸው ብለዋል።

አሁን ላይ የገጠሙ ችግሮችን በመቋቋም ፕሮጀክቱን ለመጨረስ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ የፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በኩል በሚፈጠሩ የተንዛዙ አሰራሮች ምክንያት ነው ብለዋል።

ችግሮችን በመቀራረብ ለመፍታት የተደረገው ጥረት ውጤታማ አለመሆኑንም አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡

አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የአካባቢው ማህበረሰብ የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ በመሆኑ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ለአገልግሎት መብቃት አለበት ብለዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ ለልማት ተባባሪ ነው ያሉት አቶ ታገሰ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በኩል አሉ የተባሉ ችግሮችን በተመለከተ ምክር ቤታቸው ከባለስልጣኑ ጋር በመነጋገር ይፈታዋል ብለዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የፌደራል መንግስት ቢሆንም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ለአገልግሎት እንዲበቃ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።

በስራ ወቅት ያሉ የተንዛዙ አሰራሮችንና አላስፈላጊ ቢሮክራሲዎችን ማሳጠር እንደሚገባም አሳስበዋል ሲል ደሬቴድ ዘግቧል።