የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት እና ጉህዴን የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ

ጥቅምት 9/2015 (ዋልታ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት እና በክልሉ ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የሠላምን ስምምነት ዛሬ ተፈራረሙ።

የሠላም ስምምነት ሠነዱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ሊቀ መንበር ግራኝ ጉደታ በአሶሳ ከተማ ተፈራርመዋል።

በክልሉ በመተከል፣ ካማሽ እና በተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰቱ የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና የልማት ስራዎችንም በጋራ ለመስራት ነው ከስምምነት የተደረሰው፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲው አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጉሙዝ ብሄረሰብ ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማሳደግ ተከታታይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው የጋራ የስምምነት ሰነዱ የተፈረመው።

በክልሉ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ የጉህዴን ሊቀመንበር ግራኝ ጉደታ፣ የክልሉን ሰላም ለማጠናከር የጉሙዝ ማህበረሰብ ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ጋር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችም ለክልሉ ሰላምና ለዜጎች ደህንነት ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩም አሳስበዋል ሲል ኢብኮ ዘግቧል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው የክልሉን ሁለገብ ሰላምና ልማት ለማጠናከር መላው የጉሙዝ ማህበረሰብና በፓርቲው ስም የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላትም ፊታቸውን ወደ ሰላም በማዞር ለክልሉ ሰላምና ደህንነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።