የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ መሪዎች ወቅታዊ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ አሳሰበ

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት

ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) የሶማሊያ መሪዎች ወቅታዊ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት አሳሰቡ።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በወቅታዊ የሶማሊያ መሪዎች ፖለቲካዊ አለመግባባት ዙሪያ በሰጡት መግለጫቸው የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በትኩረት እየተከታተለው ነው ብለዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሁሴን ሮብሌ በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱም አሳስበዋል፡፡

መሪዎቹ ሀገሪቱን የባሰ አደጋ ላይ ከሚጥል እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡም ነው ሙሳ ፋኪ ያስጠነቀቁት።

የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ያለው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት እንዲፈታ በላቀ ሁኔታ እንደሚሰራም ማረጋገጣቸውን ከኅብረቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።