የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦችን ወደ ግጭት ለማስገባት በሚሞክሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ ይገባል – ምሁራን

የህግ ባለሙያው አቶ ጌትነት ባንጃው

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – ለዘመናት አብረው በኖሩ፣ በተዋለዱ እና የጋራ እሴት ባላቸው የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች ላይ ልዩነት በመፍጠር ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ በሚሞክሩ አካላት ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ ዋልታ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ፡፡

ለዘመናት አብረው ተዋልደው በኖሩ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የህዝብ ለህዝብ ችግር የለም ያሉት የህግ ባለሙያው አቶ ጌትነት ባንጃው፣ የሀሰት ትርክቶችን ለማረም እና ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስም የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ምክክር እና ውይይቶች ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦችን ለመለያየት አሁን ላይ እየተሰበኩ ባሉ የሀሰት ትርክቶች በሁለቱ ብሄሮች መካከል መቃቃርን በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጥሩ የውጭ እና የውስጥ ሀይሎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ህዝቦች መካከል ምንም አይነት የጥላቻ ስሜት የለም ያሉት ደግሞ የሰብአዊ መብት እና የፌደራሊዚም መምህር እና ተመራማሪ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ህዝቡን ለጥፋት የሚያነሳሱ ድርጊቶችን እና እየተነገሩ ያሉ የሀሰት ትርክቶችን በማጥፋት ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ግን የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የሰብአዊ መብት እና የፌደራሊዚም መምህር እና ተመራማሪ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)

ሁለቱ ብሄሮችን በማለያየት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በየጊዜው ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎችን እየፈጸመ በሚገኘው የኦነግ ሸኔ ቡደን ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ነው ምህራኑ ያነሱት፡፡

(በሜሮን መስፍን)

 

shares