ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአገራዊ ወቅታዊ ዙሪያ የሰጡት ሙሉ መግለጫ
የሕዝብን ጥያቄዎች “ከጎዳና ወደ ፓርላማ” የሚወስድ ምርጫ!
የዘንድሮው ምርጫ የዘመናት ቋጠሮዎች የሚፈቱበት ቁልፍ እንደሆነ መዘንጋት ሞኝነት ነው፡፡ በሀገራችን ለበርካታ ዓመታት የሕዝቦችን ጥያቄ ወደ ተገቢው የዴሞክራሲ ባሕል መንገድ ማስገባት አልተቻለም ነበር።
ጉዳዩን ወደኋላ አርዝመን ካየነው ምናልባትም ከታኅሳሱ ግርግርና ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የሕዝባችን የፖለቲካ ጥያቄዎች በዋናነት የሚንጸባረቁት አንድም በጎዳና ላይ ዐመጽ፣ ሁለትም በጦር መሣሪያ አማካኝነት ነበር። ሁለቱም መንገዶች እጅግ ኋላቀርና አውዳሚዎች እንደ ነበሩ እስኪበቃን አይተናል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በድኻ ወገቧ አስተምራ ለከፍተኛ ደረጃ ያደረሰቻቸው አያሌ ተማሪዎች እና ምሁራን በገፍ አልቀውበታል። ለዓመታት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች በቀናት ልዩነት ወደ ትቢያነት ተለውጠዋል።
እንዲያም ሆኖ የዘመናት ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ አላገኙም። ለምን?
በአንድ በኩል ነጻ አውጭ ድርጅቶች፣ ጠብመንጃ አንሥተው በገቡበት ጫካ “ራስን በራስ የማስተዳደር የብሔሮች መብት ዛሬውኑ ይከበር” ሲሉ፤ በሌላ በኩል የከተማ ሽምቅ ውጊያ የጀመሩ ኃይሎች “ሕዝባዊ መንግሥት ዛሬውኑ” እያሉ ሲፋለሙ ነበር። ከፍልሚያው በኋላ፣ የጭቆና ቀንበር ጫነ የተባለው ድርጅት ከመንበረ ሥልጣኑ ሲገለል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቅርጥፍ አድርገው የበሉ ጥያቄዎች በወጉ መልስ ሳይቸራቸው፣ “የሞግዚት አስተዳደር” እንዲያበቃ ዳግም ወደ ጫካ፣ ዳግም ወደ ጎዳና ተወጥቷል። ለምን?
“ምርጫ 97” የሕዝብን ጥያቄ ወደ ካርድ ማምጣት የቻለ ቢሆንም፣ ሂደቱ በአግባቡ ባለመቋጨቱ ምክንያት ውጤቱ የድሮው ዓይነት የጎዳና ዐመጽና የበረሃ ትግልን ወልዷል። በጎረቤት ሀገራት ተደብቀው ኢሕአዴግን በጦር መሣሪያ ለመጣል ሲታገሉ የነበሩት ድርጅቶች እንቅስቃሴ ምንጩ ያንን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ ባለመጠቀም የተፈጠረ እንደሆነ አይካድም። መቀመጫቸውን አሜሪካና አውሮፓ ያደረጉ፣ በሳይበርና በሜንስትሪም ሚዲያዎች ታግዘው ሲከናወኑ የነበሩ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴዎች በሀገር ውስጥ ካሉ የተቃውሞ ኃይሎች ጋር በመጣመር ዜጎች ድምፃቸውን በየጎዳናው እንዲያሰሙ በመገፋፋታቸው፣ ለብዙዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። ለምን?
የእነዚህ ሁሉ “ለምን” ጥያቄዎች መልሱ የሚያጠነጥነው የሕዝብ ድምፆች ተገቢውን ቦታ አግኝተው መሰማት አለመቻላቸው ነው። በሌላ አማርኛ ፓርላማችን እውነተኛ ፓርላማ የሚያደርገውን ባህሪ እንዲላበስ ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት የተፈጠረ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ልዩ ልዩ የሕዝብ ድምፆች የሚሰሙበት ፓርላማ ኖሯት አያውቅም። ሕዝብ ድምፁ በፓርላማ የሚሰማለት ከሆነ በምን ምክንያት ሕይወቱ በየጎዳናው ወይም በየዱር ገደሉ እንዲቀጠፍ ይፈልጋል? በምንም፡፡
በዓለማችን ላይ በዴሞክራሲ ከፍ አድርገን የምንጠቅሳቸው ሀገራት የሕዝብ ጥያቄዎች የሚደመጡት በየጎዳናውና ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ሳይሆን በምክር ቤቶቻችው ነው። ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጁ ውሳኔዎች ሁሉ የሚወሰኑት በምክር ቤቶቹ አማካኝነት እንጂ በሌላ አካል አይደለም። ውሳኔውም በሀገሬው ሕዝብ ሙሉ ተቀባይነት አለው፡፡
ይሄንን ያደረገው ወደ ውሳኔው ያደረሱት ሐሳቦች የእውነት የሕዝብን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ሂደቱ አሳማኝ ስለሚሆን ጭምር ነው። ለዚህም ሕዝቡና መንግሥት ያልተጭበረበረና የዜጎችን ድምፅ በትክክሉ የሚገልጽ ምርጫ እንዲካሄድ ከምንም በላይ የተለየ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። በዚህ መልኩ አንዴ ምርጫው የተሳካ ሆኖ ከተከናወነ ሕዝቦች ወደ ጎዳና መውጣት ሳያስፈልጋቸው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ድምፃቸው ስለሚሰማላቸው፣ ዜጎቻቸው ሰፊ ጊዜያቸውን በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አውለው፣ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል።
የዘንድሮው የሀገራችን ምርጫ ለኢትዮጵያውያን ይሄንን ወርቃማ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ በተሳካ መልኩ ማከናወን ከቻልን በእርግጥም የሕዝባችንን ድምፅ ከጎዳና ወደ ፓርላማ፣ ከጫካ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ይመልሳል፡፡ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በተሳካ መልኩ ማከናወን ቢቻል፣ መንግሥት የመመሥረቻ የሚያስችል መቀመጫ (ሃምሳ ሲደመር አንድ) ካገኘው ፓርቲ ባለፈ ሌሎች ፓርቲዎች ቁጥራቸው የማይናቅ የፓርላማ መቀመጫዎችን ያገኛሉ።
ይህ ማለት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ ማለት ነው።
የሀገርን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ውሳኔዎች በጥቂት ግለሰቦች/ቡድኖች የሐሳብ የበላይነት ተፈጻሚ መሆናቸው አብቅቶ ብዙ ድምጾች ተሰምተው፣ ብዙ ክርክሮች ተደርገው፣ ብዙ ሐሳቦች ተሰጥተውበት ይወሰናል፡፡ ለዚህ መሳካት የምርጫው ሂደት ላይ የተአማኒነት ጥያቄ ሊያስነሱ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ርምጃዎች ቀድመው ተወስደዋል። ከየትኛውም ፓርቲ ፍላጎት ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ በታሪካችን የመጀመሪያው አሁን ያለው የምርጫ ቦርድ እንደሆነ ሁላችንንም ያስማማል የሚል ግምት አለኝ። ያም ሆኖ፣ ሁላችንም ካርድ ወስደን ፍቃዳችንን ሊሞላልን የሚችለውን ተወካይ እስካልመረጥን ድረስ የተሠራው ሁሉ ትርጉም የለሽ ይሆናል፡፡ ሀገራችንም የኖረችበት አዙሪት ውስጥ ትወድቃለች፡፡ ስለዚህ የዕለት ተዕለት ችግርን በዕለት ተዕለት መፍትሔ ከመጋተር፤ ዋናውን መሠረታዊ ችግር በመሠረታዊ መፍትሔ ማስወገድ አዋጭ ነው።
አንዳንዶች ምርጫውን በዚህ ሰዓት ማድረግ ቅንጦት እንደሆነ አድርገው የተለያዩ ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። በማንነታቸው ሰዎች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሽምቅ ተዋጊዎች ሰላማዊውን ሕዝብ ረፍት እየነሡት ስለ ምርጫ መጨነቅ ተገቢ አይደለም ይላሉ። ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ ጥቃቶች ከውጭ ሀገራት እየተሰነዘሩብን፣ በዚህ በኩል የኑሮ ውድነትና የኮሮና ወረርሽኝ የዕለት ተዕለት ኑሯችን ላይ አደጋ እየጋረጠብን፣ ሌላ ራስ ምታት የሚሆን፣ ተጨማሪ ቀውሶችን ሊጋብዝ የሚችል ምርጫ ማድረግ እብደት እንደሆነ ይገልጻሉ።
እነዚህ ምክንያቶች ከላይ ከላይ ሲታዩ አሳማኝና የሰዎችን ልብ የሚገዙ ቢመስሉም፣ ከላይ በሰፈሩት መነጽሮች ሲፈተሹ ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ መከራከሪያዎቹ በሀገራችን የሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ለውጭ ሀገራት ኃይሎች እና የግል ፍላጎታቸውን ለሚያሳድዱ የውስጥ ኃይሎች ካልሆነ በቀር ደካማ መንግሥት ስለኖረን ሀገራችን ምንም ነገር እንደማታተርፍ ግልጽ ነው፡፡ ሁላችንም በንቃት በምንሳተፍበት የዘንድሮው ምርጫ የሕዝቦች ጥያቄ ከጎዳና ወደ ፓርላማ መግባቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መመሥረት በመቻሉ ሀገራችን የምታገኘው ጥቅም ከላይ ለቀረበው መከራከሪያ በቂ መልስ መሆን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዚያ 17፣ 2013 ዓ.ም