ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና የሚያገለግሉ ቁሳቁስ የማድረስ ሥራ በሁለት ቀናት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

ሰኔ 02/2013 (ዋልታ) – ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና የሚያገለግሉ የስልጠና ቁሳቁስ ለምርጫ ክልሎች የማድረስ ሥራ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ ከ150 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫ ሥራን አስመልክቶ ለሚሠጠው ስልጠና የሚያገለግሉ 3 ሺህ 800 ቡል ቦክስ ለየምርጫ ክልሎች የማድረስ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የምርጫ ቁሳቁስን ጨምሮ የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ መካተታቸውን ገልጸዋል።

ቁሳቁስን ለየምርጫ ክልሎች በማድረስ ረገድ ምንም ችግር አልገጠመንም ያሉት ወ/ሪት ሶሊያና፣ ለዚህም በቂ ባይሆንም የክልል እና የፌደራል መንግስታት ትብብር አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ለድምፅ መስጫ ቀን የሚያገልግሉ ቁሳቁሶችን ለስርጭት ዝግጁ የማድረግ ስራዎችም በመከናወን ላይ እንደሚገኙና ከድምፅ መስጫ ወረቀት ውጭ ያሉ ለምርጫ ቀን የሚያገለግሉ ቁሳቁስ ስርጭት እየተካሔደ መሆኑም ተጠቁሟል።

(በድልአብ ለማ)