ለሰብዓዊ ድጋፍ ማከፋፈያ የሚውል ነዳጅ መዘረፉን መስማት ይረብሻል- ማርቲን ግሪፍትስ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) በመቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዝን ለሰብዓዊ ድጋፍ ማከፋፈያ የሚውል ነዳጅ በሽብር ቡድኑ ህወሃት መዘረፉን ተከትሎ ዓ ለም አቀፍ የቁጣ ድምጾች መሰማታቸውን ቀጥለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ እና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍትስ በዚህ የሽብር ቡድኑ እኩይ ተግባር መረበሻቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ በሕወሃት የሽብር ቡድን የተዘረፈው በ12 ታንከሮች የነበረ እና ከ570 ሺሕ ሊትር በላይ ነዳጅ በትግራይ ከልል ለሚገኙ እና አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚያስፈልጉ የምግብና መሰል ድጋፎችን ለማዳረስ በተባበሩት መንግስታት ምግብ ፕሮግራም እና አጋሮቹ  የተበረከተ መሆኑን ግሪፍትስ ጠቁመዋል፡፡

ይህ ነዳጅ በሽብር ቡድኑ ሕወሃት መዘረፉን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት በድጋፍ የተሰጠ እና መቀሌ የደረሰው ምግብ እና መድሃኒት በእጅጉ ለሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ይጎዳዋል ብለዋል፡፡

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የምግብ ዋስትና ችግር እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት የሽብር ቡድኑ ይህን ዝርፊያ መፈጸሙ መዘዙ አስከፊ ሊሆን ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሰብዓዊ ድጋፎች ላይ የሚፈጸምን ወንጀል አወግዛለሁ ያሉት አስተባባው የሰብዓዊ ድጋፍ ለተጎጂዎች እንዳይርስ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ በአፋጣኝ መቆም አለበትም ብለዋል፡፡