ለትግራይ ክልል ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ደረሰ

የአፈር ማዳበሪያ

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል ለ2013/2014 የምርት ዘመን በግብአትነት ከሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ በአካባቢው መድረሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የገበያ ልማት ዳሬይክተር አቶ ካህሳይ ሰባጋድስ እንደገለጹት፣ ወደ ክልሉ የደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ለምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 800 ሺህ ኩንታል ውስጥ ነው።

ቀሪውን በተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ ከወደብ የማስገባቱ ስራ ይጠናቀቃል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ለክልሉ የደረሰው ማዳበሪያ መቐሌ በሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት መጋዘኖች መከማቸቱን ዳይሬክተሩ ገልጸው በቅርቡም በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ልማቱ ወደሚካሄድባቸው ወረዳዎች የሚከፋፈል መሆኑን አስረድተዋል።

ማዳበሪያው ወደ ክልሉ እየገባ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሰጠው የአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ብር የብድር ዋስትና መሰረት መሆኑን አስታውቀዋል።

ለምርት ዘመኑ ጥቅም ላይ የሚውለው ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ግብአቶችን ለሚያከፋፍሉ  የህብረት ስራ ማህበራት አቅማቸውን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለማህበራቱ ማጠናከሪያ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር በተዘዋዋሪ ብድር እንዲያገኙ ሁኔታቸው መመቻቸታቸውም ተመልክቷል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኘው የበኩራ ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አትክልቲ ከበደ በበኩላቸው፤ የምርት ማሳደጊያ ግብአቱ በአካባቢያቸው ወደ ሚገኙ አርሶ አደሮች ለማድረስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አርሶ አደሮች እያቀረቡ ያሉት የማዳሪያ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከተው አካል ጋር ስምምነት መፈፀማቸውን አስረድተዋል።