ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ልዩ ትጋት ይጠይቃል- አቶ ንጉሡ ጥላሁን

              የኢፌዴሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን

የፌደራልና የክልሎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለድርሻ አካላት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ እንደ አገር የተሰሩ ሥራዎች አፈጻጸም፣ የታዩ ክፍተቶችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንዲሁም የቀጣይ 6 ወራት ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች ላይ ምክክር እየተደረገ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን መጪው ጊዜያት ከመቼውም በላይ በተቀናጀ ሁኔታ በመሥራት ለዓመቱ የተያዘውን ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድሎች የሚፈጠሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ልዩ ትጋት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

የክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት እንዲህ ባሉ መድረኮች ተገናኝተው የተሠሩ ሥራዎችን መገምገማቸው የተቀናጀ እና የተናበበ ሥራ ለመሥራት ያስችላል፤ በአመራር ደረጃም ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ያግዛልም ብለዋል ::

የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ ወሳኝ የሆኑትን የመንግስትና የግል ኢንቨስትመንት ዘርፎችን አቅጣጫ በአዳዲስ የሥራ ዘርፎች ፈጠራ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን ማዳበር እና ክህሎቶችን ማጎልበት እንዲሁም ሥራ ገበያው ፍላጎት እና አቅርቦት የሚጣጣሙበት ሁኔታ ላይ ይሰራል ተብሏል::

ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር ደረጃ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን እና አፈጻጻም የሚያመላክቱት መረጃዎች በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ምክር ቤት ተግምግሞ ከፀደቀ በኃላ ይፋ እንደሚደረግ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።