ሊዮኔል ሜሲ የፔሌን ክብረ-ወሰን ሰበረ

ሊዮኔል ሜሲ 644ኛ ጎሉን ለክለቡ ባርሴሎና በማስቆጠር የፔሌን ክብረ ወሰን ሰብሯል።

ሜሲ የከፍተኛውን ግብ ክብረ ወሰን በእጁ ለማስገባት የቻለው ቡድኑ ባርሴሎና ከሪያል ቫላዶሊድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ላይ ከመረብ ባገናኘው ጎል ነው።

በዚህም ሜሲ ለአንድ ክለብ ብዙ ጎሎች በማስቆጠር የብራዚላዊውን እግር ኳሰኛ ፔሌ ክብረ ወሰን ሰብሯል።

ማክሰኞ ምሽት ከቫላዶሊድ ጋር የነበረውን ጨዋታ የረታው ባርሴሎና ከስምንተኛ ደረጃ ወደ አምስተኛ ከፍ ያለ ሲሆን ሊዮኔል ሜሲ በትላንቱ ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።

ለ19 የውድድር ዘመኖች ለአገሩ ክለብ የተጫወተው ፔሌ 643 ጎሎች ከመረብ ማገናኘት ችሏል።