ሕጋዊ ምዝገባ ላጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት እንዲያስገቡ ጥሪ ቀረበ

                                   የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገራዊ ምርጫን ለማከናወን ሕጋዊ ምዝገባ ላጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥር 13-18 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት የምርጫ ምልክት እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርቧል።

ቦርዱ ባወጣው መረጃ መሠረት የምርጫ ምልክት መረጣው እንደሚከተለው የሚከናወን መሆኑንም አመልክቷል።

  1. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ምልክትነት ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ምልክቶችን ያዘጋጀ ሲሆን የፓርቲ ተወካዮች ከተዘጋጁት ምልክቶች ሊወክለኝ ይችላል የሚሉትን ይመርጣሉ።
  2. የመረጡት ምልክት በፓርቲያቸው የተያዘ መሆኑን ያስመዘግባሉ።

አንድ ፓርቲ ያስመዘገበው ምልክት ከሚመረጡ ምልክቶች ዝርዝር ውስጥ ይወጣል።

  1. በቦርዱ ከተዘጋጀው ምልክት ውስጥ የሚፈልጉትን ምልክት ያላገኙ ወይም የራሳቸውን ምልክት ማስመዝገብ የሚፈልጉ ፓርቲዎች የሚከተሉትን ነገሮች ማሟላት አለባቸው።

– ምልክታቸውን አትመው ለማስመዝገብ ይዘው መምጣት አለባቸው።

– የምልክታቸውን ዲጂታል ፎርማት በፍላሽ ማቅረብ አለባቸው።

– ምልክታቸው በጥቁር እና ነጭ ቀለም የተዘጋጀ መሆን አለበት።

– ምልክታቸው 2 ሲሜ በ2 ሴሜ መሆን አለበት

– የጥራት መጠኑ 200-300 ፒክስል መሆን አለበት

– የፋይሉ መጠን ቢበዛ 200 ኪሎባይት መብለጥ የለበትም

  1. የምርጫ ምልክት መረጣው የሚከናወነው ከጥር 13- 18 ሲሆን ቦርዱ ከ18-24 ባለው ጊዜ ውስጥ የማጣራት እና የመወሰን ተግባራትን ያከናውናል ተብሏል።
  2. ከጥር 13-18 ቀን 2013 በሚደረገው የምልክት መረጣ ላይ ማንኛውም ሕጋዊ ምዝገባቸውን ያጠናቀቁ ፓርቲዎች በሥራ ሰዓት ቦሌ ማተሚያ ቤት ፊት ለፊት ባለው የሺ ሕንፃ 7ኛ ፎቅ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ማእከል ይከናወናል ብሏል ቦርዱ።
  3. ይህ የምርጫ ምልክት መረጣ የግል እጩዎችን የማያካትት ሲሆን፣ የግል እጩዎች ምልክታቸው የሚመርጡበት መንገድ ወደፊት በቦርዱ የሚገለጽ መሆኑንም ቦርዱ ገልጿል።