መንግሥት ሰሞኑን መተከል ዞን ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገለጸ

መጋቢት 3/2014 (ዋልታ) ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብኣዊነት ያፈነገጠ ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ መንግሥት ገለፀ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ድርጊት መፈጸሙን አንስቷል።

በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በተንቀሳቃሽ ምስል ሲዘዋወር በቆየው እጅግ አሰቃቂ ድርጊት ንፁሃን ዜጎች በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ሲደረግ መታየቱ በመግለጫው ተመላክቷል።

ይህ ድርጊት ከኢትዮጵያዊነት ባህል፣ እሴትና ከማንኛውም የሰብዓዊነት እሳቤ ያፈነገጠና እጅግ አሰቃቂ ወንጀል ነው ያለው አገልግሎቱ ይህ እኩይ ድርጊት መጠፋፋትን ያፈጥን ካልሆነ በቀር ሰላምንም ሆነ ፍትህን እውን ሊያደርግ እንደማይችልም አስገንዝቧል።

ድርጊቱ ሊኮነንና ሊወገዝ እንደሚገባ እና መነሻቸውም ሆነ ማንነታቸው ምንም ይሁን ምን መንግስት ይህን አይነት ፍፁም ከሰብኣዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተገልጿል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ህገወጥነት ለመቆጣጠርና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከልም ከክልሉና ከመላው የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

የንፁሃን ዜጎችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን መንግሥት ከዚህ በኋላ አይታገስም ያለው መግለጫው እነዚህ በወንጀል ስራ ላይ የተሰማሩና የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም በጥብቅ አሳስቧል።