መንግሥት የምርምራ ውጤት ምክር ሀሳብን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ዝግጁነት አበረታች ነው

ግንቦት 7/2014 (ዋልታ) መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርምራ ውጤት ምክር ሀሳብን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ዝግጁነት አበረታች መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ ይፋ አድርጓል።
ምክትል ኮሚሽነሯ ራኬብ መሰለ ኮሚሽኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰብዓዊ መብትን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት አከናውኗል ብለዋል።
በዋናነትም ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ሁኔታ ምክንያት የሚያጋጥሙ የመብት ጥሰቶችን ሲመረምርና ውጤቱንም ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ መጀመሪያ በትግራይ ቀጥሎ በአፋርና አማራ ክልሎች ያጋጠሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ምርመራ መደረጉን አስታውሰዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ገለጻ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ዋና አላማ፤ ተጎጂዎች ፍትህና ካሳ እንዲያገኙ ማስቻል ነው።
በዚህ ሂደት በኮሚሽኑ በኩል የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት አበረታች ርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል ተብሏል።
ለአብነትም መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙን የመብት ጥሰት ተከትሎ የተሰጠውን ምክር ሀሳብ ለመተግበር የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ማቋቋሙን በበጎ መልኩ አንስተዋል።
ምክትል ኮሚሽነሯ ሰብዓዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ተግባራት በአንዴ የሚጠናቀቁ ሳይሆን በሂደት ለውጥ የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምንም እንኳን አንዳንድ ጉዳዮች በመንግስት በኩል ፈጣን ምላሽ ባይሰጣቸውም በአብዛኞቹ ላይ ግን የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጥቅሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተከትሎ በተደረጉ የምርመራ ውጤቶች መሰረት የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች አበረታች በሚባል መልኩ እየተተገበሩ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ያለውን የመብት ጥሰት አስመልክቶ 270 ፖሊስ ጣቢያዎች ቅኝት ማድረጉን ጠቁመዋል።
በዚህም ከ700 በላይ ያለአግባብ የታሰሩ ግለሰቦች መፈታታቸውንና ሌሎች ማስተካከያዎች መደረጋቸውንም አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሴቶችና ሕጻናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን እንዲሁም የአገር ውስጥ
ተፈናቃዮችን ማዕከል አድርጎ የሚሰራ መሆኑን መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።