መገናኛ ብዙሃን ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው ሊዘግቡ ይገባል ተባለ

                            የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሙያዊ ስነ-ምግባርን በተከተለ መልኩ ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው ሊዘግቡ ይገባል ተባለ፡፡

ባለሙያዎች ለሚያገለግሉበት ተቋም ፍላጎት ብቻ ተገዢ ከመሆን ወጥተው ለሕዝብ ሊወግኑ ይገባልም ተብሏል፡፡

በብሮድካስት ባስልጣን፣ በሰላም ሚኒስቴር፣ በዴስትኒ ኢትዮጵያና በሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አዘጋጅነት ከጥር 5 እሰከ 7 ለሶስት ቀናት የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ቁጥራቸው 50 የሚሆኑ ጋዜጠኞች፣ የመገናኛ ብዙሀን ኃላፊዎች፣ የማህበራት ተወካዮች፣ የምክር ቤት አመራሮች የተገኙበት ጉባዔ ተካሂዷል፡፡

በጉባኤው በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ መንስኤዎችና መፍትሄ ላይ ውይይት ተደርጎ በዋናነት በመገናኛ ብዙሀን ላይ የሚስተዋሉ አምስት ችግሮች ተለይተዋል፡፡

በዚህም የሙያ ነጻነት መጓደል፣ መረጃ የማግኘት መብት አለመከበር፣ ሙያና የሙያ ስነምግባር መጓደል፣ ጠንካራ የሙያ ማህበራት አለመኖርና በሀገራዊ ጥቅም ላይ ሀገራዊ መግባባት ላይ አለመድረስ ለሚሉት ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫም አስቀምጠዋል፡፡

የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ ባለሙያዎች ሙያዊ ስነምግባርን በተከተለ መልኩ ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሊዘግቡ ይገባል ብለዋል፡፡

መረጃ የማግኘት መብት አለመከበር በተደጋጋሚ የሚታይ ችግር መሆኑ የተነሳ ሲሆን ባለሙያዎች ለመብታቸው ተደራጅቶ ከመታገል ይልቅ ዳር ቆመው መመልከትን መርጠዋልም ተብሏል፡፡

የመገናኛ ብዙሀን ሀላፊዎቹም በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የድርሻቸውን ለመውሰድ፤ በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚተገበሩ እቅዶችን መንደፋቸው ታውቋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃኑ ችግር ዘርፈ ብዙ ነው በተባለለት ጉባዔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱ ተጠቁሟል፡፡

መገናኛ ብዙሀኑ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሌላ አካል እንዲፈቱ ከመጠበቅ ባሻገር በራስ ለመፍታት መሞከር ላይ ሊያተኩሩ ይገባልም ተብሏል፡፡

(መስከረም ቸርነት)