በዘንድሮ ምርጫ እድልም መከራም አለ- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
መጋቢት 21/2013 (ዋልታ) – በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ እና በሰኔ ወር መጀመሪያ በሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ እድልም መከራም አለ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ፡፡
በርካታ የውስጥም ይሁኑ የውጪ ሀይሎች ምርጫውን ተጠቅመው ሀገሪቱን ለማተራመስ ወጥነው እየሰሩ በመሆናቸው ምርጫውን ሰላማዊ በማድረግ ኢትዮጵያን አሸናፊ ልናደርጋት ይገባል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አማካኝነት በተካሄደው የአዲስ ወግ ‘ሰላምና ደህንነት በምርጫ ወቅት’ በተሰኘ መድረክ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
በቅርቡ እስራኤል አድርጋ ያለፈችውን ምርጫ ዋቢ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገሪቱ አራት ጊዜ ምርጫ እያደረገች መሪዋን መምረጥ ቢያቅታትም ያለአንዳች ድንጋይ ውርወራ በሰላም ምርጫውን ማድረግ መቻሏ ትምህርት ሊሆነን ይገባል ብለዋል፡፡
ምርጫው ይደረግ እና አይደረግ የሚል ውዝግብ ቢኖርም፤ ይህንን በግልፅ ሊወስን የሚችለው ማነው የሚለው ሌላ ጥያቄ በመሆኑ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ላለችበት ሁኔታ ምርጫውን ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ህዝቡ ማንን ለምን እንደሚመርጥ ገብቶት ሊሳተፍ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በገዢውም ይሁን በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ልምምድ እምብዛም ያለ ባለመሆኑ ሊንማር እና ሊንዘጋጅ ይገባልም ብለዋል፡፡
በዘንድሮው ምርጫ በከተሞች ድንጋይ ይዘው ሰልፍ አድርገው ሊያውኩ የሚችሉ ሀይሎች ይኖራሉ የሚል ስጋት የለኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በርካታ ኃይላት ምርጫውን ተጠቅመው ሀገሪቱን ሊያውኩ ተዘጋጅተው እየሰሩ በመሆናቸው፣ ገንዘብ ተከፍሏቸው የሚሰሩ ቅጥረኞች ሊኖሩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ አከባቢውን ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
የዘንድሮውን ምርጫ በምንም መልኩ ካለፉት ምርጫዎች ጋር ማወዳደር አይገባም ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፣ እስካሁን ከነበረው በተለየ መልኩ ከሌብነት የፀዳ ምርጫን በማድረግ ብልፅግና ከተሸነፈ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን በማስረከብ ታሪክ ይሰራል ሲሉም አክለዋል፡፡
(በድልአብ ለማ)
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የፌስቡክ ገፃችን
https://www.facebook.com/waltainfo
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የትዊተር ገፃችን
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!