ሚኒስቴሩ የግብር ስርዓትን ቀልጣፋ የሚያደርግ ስምምነት ተፈራረመ

ሰኔ 03/2013 (ዋልታ) – የገቢዎች ሚኒስቴር የግብር ከፋዮችን የግብር ስርዓት ቀልጣፋ የሚያደርግ ስምምነት ከባንኮችና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ጋር ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ ከአራት የግል ባንኮች ጋር የተፈረመ ነው፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር የህግ ተገዥነት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ፣ ስምምነቱ ከአዲስ አበባ ዉጪ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ግብር ከፋዮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲል በኤሌክትሮኒክስ የታክስ ስርአትን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በማስተሳሰር ሲሰራ መቆየቱን በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ ተናግረዋል፡፡

የግል ባንኮች ወደዚህ ስርአት እንዲቀላቀሉ መደረጉ የበለጠ አሰራሩ ለግብር ከፋዩም ሆነ ለግብር ሰብሳቢው አካል ምቹ ከማድረጉም ባሻገር ገቢን በብቃትና በወቅቱ ለመሰብሰብ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው  በበኩላቸው÷ግብር ከፋዮች በየትኛውም ቦታ ሆነው ግብራቸውን በባንክ ሲከፍሉ የመረጃ ደህንነት መጠበቅ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

አያይዘውም በበይነ መረብ ደህንነት ላይ የሚሰነዘሩ የበይነ መረብ ጥቃት አላማዎችን በማክሸፍ አሰራሩን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የተጣለባቸውን ሃገራዊ ሃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሃስ ሚሊዮን በበኩላቸው፣ በአሰራር ስርአቱ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልፀው፣ ለበለጠ ውጤታማነት ደግሞ የግል ባንኮች ወደዚህ ስርአት እንዲገቡ መደረጋቸው አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መግለፃቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።