ማህበረሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ

መጋቢት 29 /2013 (ዋልታ) – ማህበረሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ምክንያቶችን በተቀናጀ ስልት ለመፍታት እንዲቻል የመንግስት ሴክተር መሰሪያ ቤቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የጤና ሚኒስቴርና የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም ጤና ቀንን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በሚኒስቴሩ የፕሮግራም ዘርፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ኢዴታ በመግለጫቸው ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን በማዳረስና የህብረተሰብ ጤናን በማሻሻል በኩል አመርቂ ስኬቶችን እንዳስመዘገበች አመላክተዋል።
በእናቶች፤ በጨቅላ ህፃናትና ልጆችና በተላላፊ በሽታዎች በተለይም በኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ ወባ እና ቲቢ የሞት መጠን መቀነሱንም ጠቁመዋል።
መሰረታዊ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በማስፋፋት፣ የባለሙያ ቁጥር በመጨመር፣ የጤና ኤክስቴንሽንን በትምህርት ደረጃ በመሻሻል፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የአከባቢ ንፅህናን በማሻሻል በኩልም ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
የዘንድሮ የዓለም የጤና ቀን ስናከብር ህብረተሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ እና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ምክንያቶችን በተደራጀ፤ በመተባበርና በተቀናጀ ስልት ለመፍታት እንዲቻል የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ተጠሪ ተወካይ ዶክተር ኢንደራጀት ሃዛሪክ፤ የዘንድሮ የዓለመ ጤና ቀን መሪ ሃሳብ ሁሉም ሰው በየትኛውም ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት አለበት የሚለውን እሳቤ የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል።
የመንግስት አጋሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አለም አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማሳካት ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የሚሰሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓላም ጤና ድርጅት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች መልካም ጤና የማግኘት መብታቸው እንዲከበር በቁጠኝነት ይሰራልም ብለዋል።
የዓለም የጤና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ መጋቢት 29 ጤና ነክ መሪ መልዕክቶችን መሰረት አድርጎ ይከበራል።
የዘንደሮው “ፍትሃዊ እና ጤናማ ዓለም እንገንባ- ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት የሴክተሮች ተሳትፎ ወሳኝ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ በመከበር ላይ ይገኛል።
የዓለም ጤና ቀን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከሚያዚያ 7 ቀን 1948 ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።