ማህበሩ በ114 ሚሊየን ብር በኮይሻ ሎጅ ሊገነባ ነው

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – ኦሞቲክ ጠቅላላ ንግድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ114 ሚሊዮን ብር ደረጃውን የጠበቀ ሎጅ በኮይሻ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የማህበሩ የሎጆችና ሆቴሎች መምሪያ ሃላፊ አቶ አብዲ ጠና ለኢዜአ እንዳሉት ማህበሩ በገበታ ለሀገር በታቀፈው የኮይሻ ፕሮጀክት ለሚገነባው ሎጅ አምስት ሄክታር መሬት ተረክቧል።

በሶስት ምዕራፍ ለሚካሄደው ግንባታ 114 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡንና በአሁኑ ወቅት ግንባታውን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የእንግዳ ማረፊያ ናሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የያዘው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በተያዘው ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስታውቀዋል።

ኮይሻ የጨበራ ጩርጩራ ፓርክን ጨምሮ በርካታ የተፈጥሮ መስህቦች ያሉት አካባቢ በመሆኑ በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ ጉዳት በማያደርስ መስኩ ግንባታው እንደሚከናወን አቶ አብዲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመው በቀጣይ የስራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

(ምንጭ፡- ኢዜአ)