‘ማርች 8’ ሴቶች በህብረተሰቡ ውሰጥ የሚገባቸውን እውቅናና ስፍራ እንዲያገኙ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው – ሚኒስቴሩ

ማርች 8

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – የዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን “ማርች 8” ሴቶች በህብረተሰቡ ውሰጥ የሚገባቸውን እውቅናና ስፍራ እንዲያገኙ ትልቅ መሰረት የጣለ አለም አቀፍ ኩነት መሆኑን የሴቶች፣ ህፃናት ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የፆታ እኩልነትን በማስፈን ሴቶች ከነበረባቸው ድርብርብ ተጽዕኖ እንዲላቀቁና በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮችም እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ለ110ኛ ጊዜ “Women in Leadership: Achieving an equal future in a COVID-19 world” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ “የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበሰብ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ተገልጿል፡፡

የሴቶች ሁለንተናዊ መብት መከበር በተለይ እንደ ሀገር በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅዶችና በየዘርፉ የተያዙ ውጥኖች በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት እንዲሳኩ በማስቻል ረገድ የሴቶች ድርሻ የላቀ መሆኑን አጽንኦት ለመስጠት፣ ህብረተሰቡን ለማስገንዘብና ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ይህንንም ለማሳካት ሚኒስቴሩ ከመንግስትና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የዘንድሮውን ማርች-8 ከዚህ ቀደም ከነበረው አከባበር የተለየ በማድረግ ወሩን በሙሉ ሴቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ልዩ ልዩ መረሀ-ግብሮች ለማክበር ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፣ በሴቶች እኩልነትና ውሳኔ ሰጪነት፣ በልጃገረዶች ትምህርት፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት እንዲሁም በሴቶች ጥቃት ዙሪያ በማተኮር ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በአጠቃላይ ማርች 8 “የሴቶች ወር” በሚል በብሔራዊ ደረጃ እውቅና መሰጠቱ ከሀገሪቱ ህዝብ ከግማሽ በላይ ቁጥር የሚሸፍኑት ሴቶች በታሪካዊ አውዶችም ሆነ በየዘርፉ ያሉ ጅምር የልማት እቅዶችን በማሳለጥ እንዲሁም የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ በማረጋገጥ ረገድ ሚናቸው የማይተካ መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ነው የተባለው፡፡

በሌላ በኩል ሴቶች ድህነትን በማስወገድም ሆነ ልማት በማፋጠንና ስኬታማ በማድረግ ረገድ ያላቸውን የላቀ ሚና በውል በመገንዘብ በሁሉም መስኮች ያላቸው ተሳትፎ በእኩል ደረጃ እንዲጐለብትና ብቃታቸው እንዲያድግ በመደገፍና በማበረታታት ሁሉም ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሚኒስቴሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ አካባቢ በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሀገራት የተከሰተውን የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ አብዮት ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች የሰራተኛውን ጎራ ቢቀላቀሉም ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ባለመቻላቸው የተነሳ በወቅቱ ይደርስባቸው የነበረውን የመብት ረገጣና ጭቆና በመቃወም የነጻነትና እኩልነት ጥያቄን አንግበው አደባባይ በመውጣት ለአመታት ባካሄዱት የትግል እንቅስቃሴ የተገኘ የድል ቀን ሆኖ መከበር እንደጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚህም አለም አቀፉ ማህበረሰብ በሴቶች ላይ የሚታየውን ማንኛቸውንም ጭቆናና በደል ለማስቆም የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን ከማውጣት አንስቶ ማርች 8 የሴቶች ቀን ሆኖ እንዲከበር እስከመወሰን የደረሰ እርምጃ በመወሰዱ እለቱ በየአመቱ እየታወሰ እንደሚገኝ ከኢፌዴሪ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡