ምክር ቤቱ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ


ሰኔ 4/2016 (አዲስ ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ስብሰባ የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል።

ረቂቅ አዋጁን ላለፉት ሶስት ወራት በዝርዝር ሲመለከቱ የነበሩት የጤና፣ ማህበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች እና የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት የጤና፣ ማህበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀስሙ ማሞ አዋጁ ላይ የተካተቱ ዋና ዋና ሀሳቦችን በዝርዝር አቅርበዋል።

የሕዝብ በዓላት ለዜጎች ሥነ-ምግባርና ስነ-ልቦና ግንባታ እንዲሁም ለሀገርና ለህዝብ ያላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ በውሳኔ ሀሳቡ ተብራርቷል።

የሕዝብ በዓላት ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴታቸውን ጠብቀው በሰላም በድምቀት እና የዜጎችን የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነትና መተሳሰብ በሚያጎለብት ሁኔታ እንዲከበሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

የህዝብ በዓላት አከባበርና ሥርዓት ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ያለው አስተዋፅዎ ከፍተኛ መሆኑና ለሀገራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ ከመንግስት የሚጠበቀውን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ እንዲሁም በቂ የሚዲያ ሽፋን የሚሰጥ እንደሆነም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተብራርቷል።

የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ሀሳብና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አንዳንድ የሀይማኖት ተቋማት በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት እንዳላደረጉና ቅሬታ እንዳላቸው ጠቁመዋል::

በምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀስሙ ማሞ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ ያቀርቡ ሲሆን፤ ከሁሉም የሀይማኖት ተቋማት የተወከሉ የሀይማኖት አባቶች በረቂቅ አዋጁ ላይ ስለመወያየታቸው አስረድተዋል።

ነባሩ የሕዝብ በዓላት እና የዕረፍት ቀን መወሰኛ አዋጅ የሕዝብ በዓላት ሲከበሩ ጥቅም ሊያስገኙ በሚችሉ መልኩ በድምቀት የሚከበሩበትን ዝርዝር የአከባበር ሥነ-ሥርዓት አለማስቀመጡንም የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ይህ አዋጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር የሚመለከት ሲሆን፤ ክልሎች በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ህግ አውጥተው በክልል ደረጃ የሚከበሩ አዋጆችን አከባበር መወሰን እንደሚችሉም ገልፀዋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ አዋጅ ቁጥር 1334/2016 አድርጎ አጽድቆታል፡፡