ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለቄራ አንበሳ ስፖርት ማህበር የትጥቅ ድጋፍ አደረጉ

ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ
መጋቢት 25/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለቄራ አንበሳ ስፖርት ማህበር የትጥቅ ድጋፍ አደረጉ።
ምክትል ከንቲባዋ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ዋልያዎቹ፣ ከተለያዩ ባለሀብቶች እና አርቲስቶች ጋር በመሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ቄራ አልማዝዬ ሜዳ በመገኘት ለቄራ አንበሳ ስፖርት ማህበር የትጥቅ ድጋፍ አድርገዋል።
አልማዝዬ ሜዳ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራ ሜዳ መሆኑን የገለፁት ምክትል ከንቲባዋ፣ በዘመናዊ መንገድ ግንባታው ይካሄዳል ብለዋል።
ስፖርት ሰላምን፣ አንድነትን እና ወዳጅነትን በማጠናከር በኩል ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አጠቃላይ ስፖርቱን ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ቄራ እና አካባቢው የሚኖሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው፣ የአልማዝዬ ሜዳን ከዲዛይን ጥናት ጀምሮ ሙሉ የሜዳውን ግንባታ ለማካሄድ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን ለመቆም ቃል መግባታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።