ራዕይ ህዝባዊ ንቅናቄ ወደ ራዕይ ፓርቲነት ተቀየረ

ጥቅምት 5/2014 (ዋልታ) ራዕይ ንቅናቄ በመባል የሚታወቀው ቡድን ወደ ራዕይ ፓርቲነት መቀየሩን ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫው አስታውቋል።
ይህን ውሳኔ ያደረገው የትግራይ ክልሉ ህዝብ ያቀረበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ መሆኑን የፖርቲው መስራች የሆኑት አቶ ሊላይ ኃይለማሪያም ገልፀዋል።
ፖርቲው በሰባት ዋና ዋና አምዶች ላይ በመመርኮዝ እንደሚሠራ እና በትግራይ ክልልም በመግባት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የትግራይ ህዝብን ለማጥፋት እና ከኢትዮጵያውያንን ከህዝቡ ለመገንጠል እየሠራ ያለውን የትህነግ የጥፋት ቡድንን ለመታገል እና ህዝቡ እየደረሰበት ካለው እልቂት ለመታደግ ፓርቲው መቋቋሙ ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የትግራይ ህዝብን እንደመያዣ አድርጎ ሀገሪቱን ወደ ጦርነት በማስገባት የሀገሪቱን ሠላም እና ልማት ለማጥፋት እየሠራ ያለው የሕወሓት ቡድን ካልጠፋ የክልሉም ሆነ የሀገሪቱ ሠላም መመለስ የማይታሠብ በመሆኑ፤ ፓርቲው ቡድኑን እስከወዲያኛው ለመቅበር ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር በመቆም ለመታገል ዝግጁ ነው ብሏል።
ባለፉት 30 ዓመታት በትግራይ ክልል አማራጭ ፓርቲ ሳይኖር ሕወሓት ብቻውን ፈላጭ ቆራጭ በመሆን ውስን ሰዎችን ብቻ ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ህዝቡን ያላማከለ ሥርዓትን በማራመድ የትግራይ ህዝብ ምንም አይነት ተጠቃሚነት ሳያገኝ ያቆየው አንሶት አሁንም የራሱን ጥቂት ግለሠቦችን የስልጣን ጥማት ለማረጋገጥ ሲል ህዝቡን ለብዙ እልቂት፣ ርሃብ እና ችግር ያጋለጠ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያዊነት የማያስብ ጨካኝ የሽብር ቡድን በመሆኑ እስከ መጨረሻ ለመፋለም ፖርቲው ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል።
ሕወሓት ወደ ሠላም እና እርቅ ለመምጣት የሚሆን ስነልቦናም ሆነ ተፈጥሮ ስሌለው በሰው ደም ለመቀለድ ያለመ ቡድን በመሆኑ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ከመንግስት ጎን በመቆም ሊፋለመው እንደሚገባም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
በድልአብ ለማ