ሮበርት ሎዋንዶውስኪ የአመቱ የፊፋ ምርጥ ተጫዋች ተባለ

ፖላንዳዊው የፊት መስመር አጥቂ ሮበርት ሎዋንዶውስኪ የአመቱ የፊፋ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።

ፊፋ የአመቱን ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች ደረጃ ባወጣበት መርሐግብሩ ሎዋንዶውስኪ 52 ነጥብ በማምጣት ነው አሸናፊ የሆነው።

ሮበርት ሎዋንዶውስኪን በመከተል ክርስትያኖ ሮናልዶ በ38 ነጥብ ሊዮኔል ሜሲ በ35 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሌላ በኩል የማንችስተር ሲቲዋ ተከላካይ ሉሲ ብሮንዝ የመጀመሪያዋ እንግሊዛዊት በመሆን የፊፋ የአመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፋለች።

ደቡብ ኮርያዊው የቶተንሃም ተጫዋች ሰን ሆንግ ሚን በፕርሚየር ሊጉ በርንሌይ ላይ ያስቆጠራት ግብ ደግሞ የአመቱ የፑሽካሽ ምርጥ ግብ ሆና ተመርጣለች።

የፊፋ የአመቱ ምርጥ ቡድንም ይፋ የተደረገ ሲሆን አምስት ተጫዋቾች ከፕሪሚየር ሊግ ሶስት ከጀርመን ቡንደስሊጋ፤ ሁለት ከስፔን ላሊጋና አንድ ደግሞ ከጣልያን ሴሪአ ሆነው ተመርጠዋል።

እነሱም ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከር፣ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ እና ቨርጂል ቫንዳይክ ከሊቨርፑል፣ ጆሹዋ ኪሚች፣ አልፎንሶ ዴቪስ እና አጥቂው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ከባየር ሙኒክ፣ ኬቪን ዴ ብያይን ከማንችስተር ሲቲ፣ ሮናልዶ ከጁቬንቱስ፣ ራሞስ ከሪያል ማድሪድ እና ሊዮኔል ሜሲ ከባርትሴሎና ሆነዋል።

ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርገን ክሎፕ የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ሽልማትን ሲቀዳጅ፤ የባየር ሙኒኩ ማሰኑዌል ደግሞ የፊፋ የአመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኗል።

የማንችስተር ዩናይትዱ አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድ ህጻናት በትምህርት ቤቶች የምገባ እድል ማግኘት አለባቸው በሚል የሰራው በጎ ስራ በፊፋ እውቅና አሰጥቶታል።

(ምንጭ፡-ቢቢሲ ስፖርት)