ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ 1,266 ተማሪዎችን አስመረቀ

                                    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች

ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ዙር 1 ሺህ 266 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመረቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው ዩንቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በስሩ ባሉ 5 ኮሌጆች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሲሆኑ፣ 711 ወንድ እና 555 ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ በዶ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ህፈት ቤት ኃላፊ እና የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ተገኝተዋል፡፡

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገናናው ጎፌ ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በከፍተኛ ተፅዕኖ ውስጥ ምርጥ ተሞክሮዎችን መፈጸሙን ገልጸው፣ በተለይም ዩኒቨርቲውን የማደራጀት እና የምርምር ስራዎችን መስራቱን አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የመምህራን የፆታ ምጣኔ ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን በመጥቀስ፣ 17 ሴት እጩ ተመራቂዎችን በቀጥታ በመምህርነት እንደሚቀጥር ገልፀዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር 51 መድረሱን በማስታወስ፣ አሁን ሀገሪቱ ላለችበት የለውጥ ጉዞ የሚመጥን የትምህርት ዘርፍ የሚስያፈልግበት አስገዳጅ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

ኮቪድ-19 አሉታዊ ተፅዕኖ ከዳረሰባቸው ዘርፎች ዋነኛው የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ነው ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል፣ ተፅዕኖውን በመቋቋም ውጤታማ ስራ ለሰራው ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ተመራቂዎች ድህነትን በተለይም የሃሳብ ድህነትን እንዲዋጉና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፣ በአምስት ኮሌጆቹ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል፡፡

(በሳሙኤል ሀጎስ)