ሴኔቱ ዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ የመመስረቱ ሂደት ሕገ መንግሥታዊ ነው አለ

                                    ዶናልድ ትራምፕ

የአሜሪካ ሴኔት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ መመስረቱ ሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት የክስ ሂደቱን አስቀጠለ።

የትራምፕ ጠበቆች በበኩላቸው, ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሃውስን ከለቀቁ በኋላ መሰል ክስ ሊቀርብባቸው አይችልም ሲሉ ተከራክረዋል።

ይሁን እንጂ 56 በ44 በሆነ የድምጽ ብልጫ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ ክስ የመመስረቱ ሂደት ድጋፍ አግኝቷል።

ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ወር ደጋፊዎቻቸው በካፒቶል ሂላ ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ አመጽ ቀስቅሰዋል በሚል እየተወነጀሉ ነው፡፡

ትራምፕ ምንም አይነት ማረጋገጫ ሳያቀርቡ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲሉ መቆየታቸውም ይታወሳል።

ትራምፕን እየከሰሱ የሚገኙት ዴሞክራቶች ሂድቱን በኤግዚቢትነት ያቀረቧቸውን ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማሳየት ጀምረዋል።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው ወደ ካፒቶል ሂል እንዲሄዱ ‘ሲያነሳሱ’ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሂልን ሰብረው ሲገቡ፤ በንብረት እና በጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ያሳያል።

ዴሞክራቶች ባቀረቡት ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው ‘እስከመጨረሻው እንዲታገሉ’ መልዕክት ሲያስተላልፉ፤ ይህን ተከትሎም በካፒቶል ሂል ላይ ጉዳት ሲደርስ አስመልክተዋል።

ዴሞክራቱ ጄሚ ራስኪን፤ ይህ ተግባር ትራምፕን በወንጀል ማስጠየቅ አለበት ብለው ተከራክረዋል።

“ይህ የአሜሪካ የወደፊት እጣ መሆን የለበት። በመንግሥታችን ላይ አመጽ የሚቀሰቅስ ፕሬዝዳንት ሊኖረን አይገባም” ብለዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ዶናልድ ትራምፕን በዚህ ሂደት ውስጥ ማሳለፍ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት ተከራክረዋል። ዴሞክራቶችም ይህን እያደረጉ ያሉት ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ነው ብለዋል።

56-44 የሚለው የድምጽ ውጤት ስድስት የትራምፕ ፓርቲ አባላት የሆኑ ሪፐብሊካኖች ከዴሞክራቶች ጎን በመሆን ድምጽ መስጠታቸውን ያመላክታል።

በትራምፕ ላይ ክስ ለመመስረት 100 መቀመጫ ባሉት ሴኔት ውስጥ 2/3ኛ ድጋፍ ያስፈልጋል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ትራምፕ ላይ ክስ እንዲመሰረት ከተወሰነ ዶናልድ ትራምፕ ወደፊት የፖለቲካ ተሳትፎ አድርገው ስልጣን እንዳይዙ ሊደረጉ ይችላሉ።