ቋሚ ኮሚቴው የግብርና ምርምር ግኝቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ መሠራት እንዳለበት አሳሰበ

ታኅሣሥ 7/2015 (ዋልታ) በግብርናው ዘርፍ በምርምር የተረጋገጡ ግኝቶችን ወደ ተግባር በመቀየር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሠራት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሪፎርም ስራዎች ያለበትን ደረጃ ገምግሟል።

በዘርፉ የሚሠሩ የምርምር ስራ ጥንካሬዎችንና ውስንነቶችን በተመለከተ ከማዕከሉ ኃላፊዎች ጋር የተወያየው ቋሚ ኮሚቴ የማዕከሉን የስራ እንቅስቃሴን ተዘዋውሮ በመጎብኘትም ግብረ-መልስ ሰጥቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ሀሙድ ገዓስ በምርምር ተቋሙ በጥናት የተገኙ ግኝቶች ሂደቱን፣ ዘር የማባዛት ስርዓት እንዲሁም ፖሊሲና ደንቦችን በማሻሻል በሀገር ደረጃ የሚታዩ ችግሮችን በምርምር መፍታት እንዳሚገባ ተናግረዋልⵆ

የግብርና ምርምር ማዕከላት በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማድረግ አዳድስ ዝርያዎችን በመጠን፣ በአይነት፣ በጥራትና በአነስተኛ ወጪ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም አሳስቧል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቲ (ዶ/ር) በዋና መስሪያ ቤት ተጠሪ በሆኑ የምርምር ማዕከላት በሰብል፣ በፍራፍሬ፣ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል እና በተፈጥሮ ኃብት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን መናገራቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured