በሀይሌ ጋርመንት አካባቢ እየተገነባ ያለው የገበያ ማዕከል ግንባታ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሀይሌ ጋርመንት አካባቢ ወደ አንድ ቢሊየን ብር በሚጠጋ የኮንትራት ዋጋ እየሰራ የሚገኘውን ተለዋጭ የአትክልት ተራ የገበያ ማዕከል የግንባታ ሥራ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚያጠናቀቅ አስታውቋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀቢቢ መስቀላ ኮርፖሬሽኑ የገበያ ማዕከሉን በሁለት ምዕራፍ ከፋፍሎ እየገነባ መሆኑን ገልጸው፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ 14 የገበያ ሸዶች፣ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የፓርኪንግና የአረንጓዴ ቦታዎች፣ መጋዘኖች፣ የአስተዳደር ህንጻዎች እና ሌሎች የግንባታ ስራዎች እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የገበያ ማዕከሉን ከ999 ሚሊየን 886 ሺህ 603 ብር የኮንትራት ዋጋ ለመገንባት ከአዲስ አበባ የኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር በመፈራረም የግንባታ ስራውን ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም መጀመሩን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚገነቡትን የመገበያያ ሼዶች ከ70 በመቶ በላይ ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉ 80 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሸፍን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚገነቡት 14 ሼዶች ውስጥ በ588 የመገበያያ ሱቆች እንዳሉት፣ ሼዶቹ 70 ሜትር በ6  ነጥብ 6 ሜትር ስፋት በ14ቱ ሼዶች ውስጥ ያሉት 588 የመገበያያ ሱቆች ደግሞ ሶስት ሜትር በ ሶስት ሜትር ስፋት እንዳላቸው የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡