በመቀሌ ከ25 ሺህ በላይ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ የኤሌክትሪክ መስመር እየተዘረጋ ነው

ግንቦት 26 / 2013 (ዋልታ) – በመቀሌ ከተማ አዳዲስ መንደሮች ለሚገኙ ከ25 ሺህ ለሚበልጡ ቤቶች የሚያገለግል አዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት በ405 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው በ19 አዳዲስ የከተማዋ መንደሮች ይከናወናል።
በሰኔ ወር ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሮጀክቱ ከ25 ሺህ የሚበልጡ አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ምሰሶዎችን የመትከልና የመብራት ቆጣሪ ወደ መኖሪያ ቤቶች ማስገባትን ጨምሮ አፈጻጸሙ 71 ከመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በሚቀጥለው የበጀት ዓመት በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች 320 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ መስመር ጥገናና አዲስ ፕሮጀክት ግንባታ ለማካሄድ የሚውል ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ጥያቄ ለፌዴራል ኤሌክትሪክ አገልግሎት መቅረቡንም ጠቅሰዋል።
በ19ኙ መንደሮች እየተተከለ የሚገኘው ምሰሶና እየተዘረጋ ያለው መስመር ጥራቱን የጠበቀና ለ35 ዓመታት ያህል ያለ ምንም ችግር አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በፅህፈት ቤቱ የኮንትራት አስተዳደር ክፍል ሃላፊ አቶ ፀጋይ ኪዳነ ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው የምሰሶ ተከላ በማህበር በተደራጁ ወጣቶች አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመቀሌ የገፊሕ ገረብ መንደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዝርጋታ ፕሮጀክት ስራ አስከያጅ ወጣት ብርሃነ ደስታ እንደገለጸው ፕሮጀክቱ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ ነው።
ፕሮጀከቱ በእቃ አቅርቦት ውስንነትና በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት በስራቸው ላይ እንቅፋት እያጋጠማቸው በመሆኑ በጊዜው ሊፈቱ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።