በመዲናዋ ከኮቪድ-19 ክትባት ጋር ተያይዞ እየቀረቡ ያሉ አሉባልታዎችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኮቪድ-19 በከተማዋ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ እና ከክትባት ጋር ተያይዞ እየቀረቡ ያሉ አሉባልታዎችን መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ከአንድ ዓመት በፊት ቫይረሱ ወደ ኢትየጵያ ሲገባ ሁሉም ተደናግጦ እንደነበርና በከፍተኛ ሁኔታ ጥንቃቄ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በወቅቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ባደረገው አስተዋፅኦ በቫይረሱ የሚደርሰውን የሞት መጠን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ግን ጥንቃቄዎች እየተደረጉ ባለመሆኑ የሃይማኖት አባቶች እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በመነሻው ሲያደርጉት የነበረውን የግንዛቤ ማስጨበጫ አሁንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አዲስ ነገርን አስተዋውቆ ወደ ስራ መግባት ፈታኝ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጃንጥራር፣ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዘው የሚነሱ ውዥንብሮች ተገቢነት የሌላቸው መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፣ ክትባቱ ለጤና ባለሙያዎች፣ ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ አረጋዊያንና በሂደት ደግሞ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲደርስ በሚደረገው ጥረት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ ከኮቪድ-19 ራሳችንን ለመጠበቅ ወሳኙ መፍትሄ መከላከል ነው በማለት ከመከላከያ ዘዴዎቹ ቀዳሚው ክትባት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ክትባት ተመርቶ ለድሃ ሀገራት እንዲከፋፈል ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ በመግለፅም ይሄን ወርቃማ ዕድል ልንጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡

በተፈጠሩ ውዥንብሮችና አሉባልታዎች ምክንያትም ለመከተብ ከታቀደው የጤና ባለሙያ 64 በመቶውን ብቻ ለመከተብ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በቀረበ አውደ ጥናት እስካሁን በአለማችን ላይ በ154 ሀገራት ለ748 ሚሊየን ዜጎች የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽ መደረጉ እና እስካሁን በክትባቱ ሳቢያ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ነው የተጠቀሰው፡፡

ክትባቱ እንደማንኛውም ክትባት ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካምን የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል ከመቻሉ ባሻገር የተለየ ጉዳት እንደማያደርስም ነው የተገለፀው፡፡

በአዲስ አበባ በአስሩ ክፍለ ከተሞች ለመከተብ ከታሰበው 38 ሺህ 475 የጤና ባለሙያና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኛ 2 4ሺህ 109 መከተብ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ህንድ ከሚገኘው ሴረም ኢንስቲትዩት በመጀመሪያ ዙር 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የአስትራዜኒካ ክትባቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባች ሲሆን፣ በመጪው ግንቦት ወር 7 ነጥብ 62 ክትባቶችን እንደምታስገባም ይጠበቃል፡፡

(በሳሙኤል ሀጎስ)